1ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ወደ፡ኤርምያስ፡የመጣው፡ቃል፡ይህ፡ነው፦
2የዚህን፡ቃል፡ኪዳን፡ቃል፡ስማ፥ለይሁዳም፡ሰዎች፡በኢየሩሳሌምም፡ለሚኖሩ፡ተናገር፥ 3-
4እንደዚህም፡በላቸው፦የእስራኤል፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ከግብጽ፡አገር፡ከብረት፡ ምድጃ፡ባወጣዃቸው፡ቀን፡ለአባቶቻችኹ፡ያዘዝኹትን፡የዚህን፡ቃል፡ኪዳን፡ቃል፡የማይሰማ፡ሰው፡ርጉም፡ ይኹን፤አልኹም፦ቃሌን፡ስሙ፥ያዘዝዃችኹንም፡ዅሉ፡አድርጉ፤እንዲሁም፡እናንተ፡ሕዝብ፡ትኾኑኛላችኹ፡ እኔም፡አምላክ፡እኾናችዃለኹ።
5ይህም፡ዛሬ፡እንደ፡ኾነ፡ወተትና፡ማር፡የምታፈሰ፟ውን፡ምድር፡እሰጣቸው፡ዘንድ፡ለአባቶቻችኹ፡ የማልኹትን፡መሐላ፡አጸና፡ዘንድ፡ነው።እኔም፦አቤቱ፥አሜን፡ብዬ፡መለስኹለት።
6እግዚአብሔርም፡እንዲህ፡አለኝ፦ይህችን፡ቃል፡ዅሉ፡በይሁዳ፡ከተማዎችና፡በኢየሩሳሌም፡አደባባይ፡ ተናገር፥እንዲህም፡በል፦የዚህን፡ቃል፡ኪዳን፡ቃል፡ስሙ፡አድርጉትም።
7አባቶቻችኹን፡ከግብጽ፡ምድር፡ካወጣኹበት፡ቀን፡ዠምሮ፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፥በማለዳ፡ተነሥቼ፡ እያስጠነቀቅኹ።ቃሌን፡ስሙ፡በማለት፡አስጠንቅቄያቸው፡ነበር።
8እነርሱ፡ዅሉ፡ግን፡በክፉ፡ልባቸው፡እልከኝነት፡ኼዱ፡እንጂ፥አልሰሙም፥ዦሯቸውንም፡ አላዘነበሉም፤ስለዚህ፥ያዘዝዃቸውን፡እነርሱም፡ያላደረጉትን፡የዚህን፡ቃል፡ኪዳን፡ቃል፡ዅሉ፡ አመጣኹባቸው።
9እግዚአብሔርም፡እንዲህ፡አለኝ፦በይሁዳ፡ሰዎችና፡በኢየሩሳሌም፡በሚኖሩ፡ዘንድ፡ዐድማ፡ተገኝቷል።
10ቃሌንም፡ይሰሙ፡ዘንድ፡እንቢ፡ወዳሉ፡ወዳባቶቻቸው፡ኀጢአት፡ተመለሱ፥ያመልኳቸውም፡ዘንድ፡ እንግዳዎችን፡አማልክት፡ተከተሉ፤የእስራኤል፡ቤትና፡የይሁዳ፡ቤት፡ከአባቶቻቸው፡ጋራ፡ያደረግኹትን፡ቃል፡ ኪዳን፡አፈረሱ።
11ስለዚህ፥እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እንሆ፥ሊያመልጡት፡የማይችሉትን፡ክፉ፡ነገር፡ አመጣባቸዋለኹ፥ወደ፡እኔም፡ይጮኻሉ፤እኔም፡አልሰማቸውም።
12በይሁዳም፡ከተማዎችና፡በኢየሩሳሌም፡የሚኖሩ፡ኼደው፡ወደሚያጥኑላቸው፡አማልክት፡ይጮኻሉ፤ነገር፡ ግን፥በመከራቸው፡ጊዜ፡ከቶ፡አያድኗቸውም።
13ይሁዳ፡ሆይ፥አማልክትኽ፡እንደ፡ከተማዎችኽ፡ቍጥር፡እንዲሁ፡ናቸው፤እንደ፡ኢየሩሳሌምም፡መንገዶች፡ ቍጥር፡ለነውረኛ፡ነገር፡መሠዊያ፥ርሱም፡ለበዓል፡ታጥኑበት፡ዘንድ፡መሠዊያ፥አድርጋችዃል። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
14አንተም፡ስለዚህ፡ሕዝብ፡አትጸልይ፤ከመከራቸው፡የተነሣ፡ወደ፡እኔ፡በጮኹ፡ጊዜ፡አልሰማቸውምና፡ስለ፡ እነርሱም፡ጩኸትና፡ልመና፡አታድርግ።
15ወዳጄ፡በቤቴ፡ውስጥ፡ምን፡አላት፧ስእለት፡ወይም፡የተቀደሰ፡ሥጋ፡ክፋትሽን፡ከአንቺ፡ ያስወግዳልን፧ወይስ፡በእነዚህ፡ታመልጫለሽን፧
16እግዚአብሔር፡ስምሽን፦በመልካም፡ፍሬ፡የተዋበች፡የለመለመች፡የወይራ፡ዛፍ፡ብሎ፡ጠራው፤በጽኑ፡ ዐውሎ፡ነፋስ፡ጩኸት፡እሳትን፡አነደደባት፥ቅርንጫፎቿም፡ተሰብረዋል።
17ለበዓልም፡በማጠናቸው፡ያስቈጡኝ፡ዘንድ፡ለራሳቸው፡ስለሠሯት፡ስለእስራኤልና፡ስለይሁዳ፡ቤት፡ክፋት፡ የተከለሽ፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡ክፉን፡ነገር፡ተናግሮብሻል።
18እግዚአብሔርም፡አስታወቀኝ፡እኔም፡ዐወቅኹ፤ሥራቸውንም፡ገለጥኽልኝ።
19እኔም፡ለመታረድ፡እንደሚነዳ፡እንደ፡የዋህ፡በግ፡ጠቦት፡ኾንኹ፤እነርሱም፦ዛፉን፡ከፍሬው፡ጋራ፡ እንቍረጥ፥ስሙም፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡እንዳይታሰብ፡ከሕያዋን፡ምድር፡እናጥፋው፡ብለው፡ምክርን፡ እንዳሰቡብኝ፡አላወቅኹም፡ነበር።
20ኵላሊትንና፡ልብን፡የምትፈትን፡በቅንም፡የምትፈርድ፡አቤቱ፡የሰራዊት፡ጌታ፡ሆይ፥ክርክሬን፡ ገልጬልኻለኹና፡በእነርሱ፡ላይ፡የሚኾን፡በቀልኽን፡ለይ።
21ስለዚህም፦በእጃችን፡እንዳትሞት፡በእግዚአብሔር፡ስም፡ትንቢት፡አትናገር፡ብለው፡ነፍስኽን፡ስለሚሹ፡ ስለዐናቶት፡ሰዎች፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እንሆ፥እቀጣቸዋለኹ፤
22ጐበዛዝታቸው፡በሰይፍ፡ይሞታሉ፥ወንዶችና፡ሴቶች፡ልጆቻቸውም፡በራብ፡ይሞታሉ፤በምጐበኛቸውም፡ ዓመት፡በዐናቶት፡ሰዎች፡ላይ፡ክፉ፡ነገር፡አመጣባቸዋለኹና፡ማንም፡ከነርሱ፡የሚቀር፡የለም።