1ወደ፡ኤርምያስ፡ስለ፡ድርቅ፡የመጣው፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡ይህ፡ነው፦
2ይሁዳ፡አለቀሰች፥ደጆቿም፡ባዶ፡ኾኑ፡በምድርም፡ላይ፡ጨለሙ፤የኢየሩሳሌም፡ጩኸት፡ከፍ፡ከፍ፡ ብሏል።
3ታላላቆችም፡ብላቴናዎቻቸውን፡ወደ፡ውሃ፡ሰደዱ፤ወደ፡ጕድጓድ፡መጡ፡ውሃም፡አላገኙም፥ዕቃቸውንም፡ ባዶውን፡ይዘው፡ተመለሱ፤ዐፈሩም፡ተዋረዱም፡ራሳቸውንም፡ተከናነቡ።
4በምድር፡ላይ፡አልዘነበምና፡መሬቱ፡ስንጥቅጥቅ፡ስለ፡ኾነ፡ዐራሾች፡ዐፈሩ፥ራሳቸውንም፡ተከናነቡ።
5ዋላ፡ደግሞ፡በምድረ፡በዳ፡ወለደች፥ሣርም፡የለምና፡ግልገሏን፡ተወች።
6የሜዳ፡አህያዎችም፡በወና፡ኰረብታ፡ላይ፡ቆመዋል፥እንደ፡ቀበሮም፡ወደ፡ነፋስ፡አለከለኩ፤ልምላሜም፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org የለምና፡ዐይኖቻቸው፡ጠወለጉ።
7አቤቱ፥ኀጢአታችን፡ብዙ፡ነውና፥ባንተም፡ላይ፡ኀጢአት፡ሠርተናልና፥ኀጢአታችን፡ ይመሰክርብናል፥ነገር፡ግን፥ስለ፡ስምኽ፡ብለኽ፡አድርግ።
8አንተ፡የእስራኤል፡ተስፋ፡ሆይ፡በመከራም፡ጊዜ፡የምታድነው፥በምድር፡እንደ፡እንግዳ፥ወደ፡ማደሪያ፡ ዘወር፡እንደሚል፡መንገደኛ፡ስለ፡ምን፡ትኾናለኽ፧
9እንዳንቀላፋ፡ሰው፡ሰው፥ያድንም፡ዘንድ፡እንደማይችል፡ኀያል፡ስለ፡ምን፡ትኾናለኽ፧አንተ፡ ግን፥አቤቱ፥በመካከላችን፡ነኽ፡እኛም፡በስምኽ፡ተጠርተናል፤አትተወን።
10እግዚአብሔር፡ለዚህ፡ሕዝብ፡እንዲህ፡ይላል፦መቅበዝበዝን፡ወደ፟ዋል፥እግራቸውንም፡ አልከለከሉም፤ስለዚህ፥እግዚአብሔር፡በእነርሱ፡ደስ፡አይለውም፥በደላቸውንም፡አኹን፡ ያስባል፥ኀጢአታቸውንም፡ይቀጣል።
11እግዚአብሔርም፦ለዚህ፡ሕዝብ፡ስለ፡መልካም፡አትጸልይላቸው።
12በጾሙ፡ጊዜ፡ጸሎታቸውን፡አልሰማም፤የሚቃጠለውን፡መሥዋዕትና፡የእኽሉን፡ቍርባን፡ባቀረቡ፡ጊዜ፡ አልቀበላቸውም፤በሰይፍና፡በራብ፡በቸነፈርም፡አጠፋቸዋለኹ፡አለኝ።
13እኔም፦ጌታ፡እግዚአብሔር፡ሆይ፥ወዮ! እንሆ፥ነቢያት።በእውነት፡ሰላምን፡በዚህ፡ስፍራ፡እሰጣችዃለኹ፡ እንጂ፡ሰይፍን፡አታዩም፥ራብም፡አያገኛችኹም፡ይሏቸዋል፡አልኹ።
14እግዚአብሔርም፡እንዲህ፡አለኝ፦ነቢያቱ፡ውሸት፡በስሜ፡ትንቢት፡ ይናገራሉ፤አላክዃቸውም፥አላዘዝዃቸውም፥አልተናገርዃቸውም፤የውሸቱን፡ራእይ፡ሟርትንም፡ከንቱንም፡ነገር፡ የልባቸውንም፡ሽንገላ፡ይሰብኩላችዃል።
15ስለዚህ፥እግዚአብሔር፡በስሜ፡ትንቢት፡ስለሚናገሩ፡ነቢያት፦በዚች፡አገር፡ሰይፍና፡ራብ፡አይኾንም፡ ስለሚሉ፡ስላላ፟ክዃቸው፡ነቢያት፡እንዲህ፡ይላል፦እነዚያ፡በሰይፍና፡በራብ፡ይጠፋሉ።
16ትንቢት፡የሚናገሩላቸውም፡ሰዎች፡ከራብና፡ከሰይፍ፡የተነሣ፡በኢየሩሳሌም፡አደባባይ፡ ይበተናሉ፤ክፋታቸውንም፡አፈስ፟ባቸዋለኹ፡እነርሱንና፡ሚስቶቻቸውን፡ወንዶችና፡ሴቶች፡ልጆቻቸውንም፡ የሚቀብራቸው፡አይገኝም።
17እንደዚህም፡ብለኽ፡ትነግራቸዋለኽ፦የወገኔ፡ልጅ፡ድንግሊቱ፡በታላቅ፡ስብራትና፡እጅግ፡ክፉ፡በኾነ፡ ቍስል፡ተሰብራለችና፡ዐይኖቼ፡ሌሊትና፡ቀን፡ሳያቋርጡ፡እንባ፡ያፈሳሉ።
18ወደ፡ሜዳ፡ብወጣ፥እንሆ፥በሰይፍ፡የሞቱ፡አሉ፤ወደ፡ከተማም፡ብገባ፥እንሆ፥በራብ፡የከሱ፡ አሉ፤ነቢዩና፡ካህኑም፡ወደማያውቋት፡አገር፡ኼደዋልና።
19በእውኑ፡ይሁዳን፡ፈጽመኽ፡ጥለኸዋልን፧ነፍስኽስ፡ጽዮንን፡ጠልታታለችን፧ስለ፡ምን፡መታኸን፧ፈውስስ፡ ስለ፡ምን፡የለንም፧ሰላምን፡በተስፋ፡ተጠባበቅን፥መልካምም፡አልተገኘም፤ፈውስን፡በተስፋ፡ ተጠባበቅን፥እንሆም፥ድንጋጤ፡ኾነ።
20አቤቱ፥ባንተ፡ላይ፡ኀጢአትን፡ሠርተናልና፥ክፋታችንንና፡የአባቶቻችንን፡በደል፡እናውቃለን።
21ስለ፡ስምኽ፡ብለኽ፡አትናቀን፥የክብርኽንም፡ዙፋን፡አታስነውር፤ከእኛ፡ጋራም፡ያደረግኸውን፡ቃል፡ ኪዳንኽን፡ዐስብ፡እንጂ፡አታፍርስ።
22በእውኑ፡በአሕዛብ፡ጣዖታት፡መካከል፡ያዘንብ፡ዘንድ፡የሚችል፡ይገኛልን፧ወይስ፡ሰማይ፡ዝናብ፡ ማፍሰስ፡ይችላልን፧አቤቱ፡አምላካችን፡ሆይ፥አንተ፡አይደለኽምን፧አንተ፡ይህን፡ነገር፡ዅሉ፡ አድርገኻልና፥ስለዚህ፡አንተን፡በተስፋ፡እንጠባበቃለን።