2ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ወደ፡ኤርምያስ፡የመጣ፡ቃል፥እንዲህም፡አለው፦ተነሥተኽ፡ወደሸክላ፡ሠሪው፡ ቤት፡ውረድ፥በዚያም፡ቃሌን፡አሰማኻለኹ።
3ወደሸክላ፡ሠሪው፡ቤትም፡ወረድኹ፥እንሆም፥ሥራውን፡በመንኰራኵር፡ላይ፡ይሠራ፡ነበር።
4ከጭቃም፡ይሠራው፡የነበረ፡ዕቃ፡በሸክላ፡ሠሪው፡እጅ፡ተበላሸ፥ሸክላ፡ሠሪውም፡እንደ፡ወደደ፡መልሶ፡ ሌላ፡ዕቃ፡አድርጎ፡ሠራው።
5የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ወደ፡እኔ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
6የእስራኤል፡ቤት፡ሆይ፥ይህ፡ሸክላ፡ሠሪ፡እንደሚሠራ፡በእውኑ፡እኔ፡በእናንተ፡ዘንድ፡መሥራት፡ አይቻለኝምን፧እንሆ፥ጭቃው፡በሸክላ፡ሠሪ፡እጅ፡እንዳለ፥እንዲሁ፡እናንተ፡በእኔ፡እጅ፡አላችኹ።
7ስለ፡ሕዝብ፡ስለ፡መንግሥትም፡እነቅል፡አፈርስም፡አጠፋም፡ዘንድ፡በተናገርኹ፡ጊዜ፥
8ይህ፡ስለ፡ርሱ፡የተናገርኹበት፡ሕዝብ፡ከክፋቱ፡ቢመለስ፥እኔ፡አደርግበት፡ዘንድ፡ካሰብኹት፡ክፉ፡ነገር፡ እጸጸታለኹ።
9ስለ፡ሕዝቡም፡ስለ፡መንግሥትም፡እሠራውና፡እተክለው፡ዘንድ፡በተናገርኹ፡ጊዜ፥
10በፊቴ፡ክፉን፡ነገር፡ቢያደርግ፡ቃሌንም፡ባይሰማ፥እኔ፡አደርግለት፡ዘንድ፡ስለተናገርኹት፡መልካም፡ነገር፡ እጸጸታለኹ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
11አኹን፡እንግዲህ፡ለይሁዳ፡ሰዎችና፡በኢየሩሳሌም፡ለሚቀመጡ።እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ ይላል፦እንሆ፥ክፉ፡ነገር፡እፈጥርባችዃለኹ፥ዐሳብንም፡ዐስብባችዃለኹ፤አኹንም፡ዅላችኹ፡ከክፉ፡ መንገዳችኹ፡ተመለሱ፥መንገዳችኹንና፡ሥራችኹንም፡አቅኑ፡ብለኽ፡ተናገራቸው።
12እነርሱ፡ግን፦እንጨክናለን፤ዐሳባችንን፡ተከትለን፡እንኼዳለን፡ዅላችንም፡እንደ፡ክፉው፡ልባችን፡ እልከኝነት፡እናደርጋለን፡አሉ።
13ስለዚህ፥እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በአሕዛብ፡መካከል፦እንዲህ፡ያለ፡ነገር፡ማን፡ ሰምቷል፧ብላችኹ፡ጠይቁ።የእስራኤል፡ድንግል፡በጣም፡የሚያስደነግጠውን፡ነገር፡አድርጋለች።
14በእውኑ፡የሊባኖስ፡በረዶ፡የምድረ፡በዳውን፡ድንጋይ፡ይተዋልን፧ወይስ፡ከሩቅ፡የምትመጣው፡ቀዝቃዛዪቱ፡ ፈሳሽ፡ውሃ፡ትደርቃለችን፧
15ሕዝቤ፡ግን፡ረስተውኛል፡ለከንቱ፡ነገርም፡ዐጥነዋል፤ከመንገዱም፡ተሰናክለዋል፡ከቀድሞውም፡ጐዳና፡ ርቀው፡ወዳልተሠራው፡ወደ፡ጠማማው፡መንገድ፡ፈቀቅ፡ብለዋል።
16ምድራቸውን፡ለመደነቂያና፡ለዘለዓለም፡ማፏጫ፡አድርገዋል፤የሚያልፍባት፡ዅሉ፡ይደነቃል፥ራሱንም፡ ያነቃንቃል።
17በጠላት፡ፊት፡እንደ፡ምሥራቅ፡ነፋስ፡እበትናቸዋለኹ፥በጥፋታቸውም፡ቀን፡ዠርባዬን፡እንጂ፡ፊቴን፡ አላሳያቸውም።
18እነርሱም፦ሕግ፡ከካህን፥ምክርም፡ከጠቢብ፥ቃልም፡ከነቢይ፡አይጠፋምና፡ኑ፥በኤርምያስ፡ላይ፡ዐሳብን፡ እናስብ።ኑ፥በምላስ፡እንምታው፥ቃሉንም፡ዅሉ፡አናድምጥ፡አሉ።
19አቤቱ፥አድምጠኝ፥የክርክሬንም፡ቃል፡ስማ።
20ለነፍሴ፡ጕድጓድ፡ቈፍረዋልና፥በእውኑ፡በመልካም፡ፋንታ፡ክፉ፡ይመለሳልን፧ስለ፡እነርሱ፡በመልካም፡ እናገር፡ዘንድ፡ቍጣኽንም፡ከነርሱ፡እመልስ፡ዘንድ፡በፊትኽ፡እንደ፡ቆምኹ፡ዐስብ።
21ስለዚህ፥ልጆቻቸውን፡ለራብ፡ስጥ፥ለሰይፍም፡እጅ፡አሳልፈኽ፡ስጣቸው፥ሚስቶቻቸውም፡የወላድ፡ መካንና፡መበለቶች፡ይኹኑ፥ወንዶቻቸውም፡በሞት፡ይጥፉ፥ጕልማሳዎቻቸውም፡በሰልፍ፡ጊዜ፡በሰይፍ፡ ይመቱ።
22ሊይዙኝ፡ጕድጓድ፡ቈፍረዋልና፥ለእግሮቼም፡ወጥመድ፡ሸሽገዋልና፥ድንገት፡በላያቸው፡ጭፍራ፡ ባመጣኽ፡ጊዜ፡ከቤታቸው፡ጩኸት፡ይሰማ።
23አንተ፡ግን፥አቤቱ፥ይገድሉኝ፡ዘንድ፡በላዬ፡የመከሩትን፡ምክር፡ዅሉ፡ታውቃለኽ፤በደላቸውን፡ይቅር፡ አትበል፥ኀጢአታቸውንም፡ከፊትኽ፡አትደምስስ፤በፊትኽም፡ይውደቁ፥በቍጣኽ፡ጊዜ፡እንዲሁ፡አድርግባቸው።