1እግዚአብሔርም፡እንዲህ፡አለኝ፦ኺድ፥ከሸክላ፡ሠሪ፡ገምቦ፡ግዛ፥ከሕዝቡም፡ሽማግሌዎችና፡ከካህናት፡ ሽማግሌዎች፡ከአንተ፡ጋራ፡ውሰድ፤
2በካርሲት፡በር፡መግቢያ፡አጠገብ፡ወዳለው፡ወደሄኖም፡ልጅ፡ሸለቆ፡ኺድ፥በዚያም፡የምነግርኽን፡ቃል፡ ተናገር፥
3እንዲህም፡በል፦የይሁዳ፡ነገሥታትና፡በኢየሩሳሌም፡የምትኖሩ፡ሆይ፥የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ ስሙ፤የእስራኤል፡አምላክ፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦የሰማውን፡ሰው፡ዦሮ፡ጭው፡ የሚያደርግ፡ክፉ፡ነገር፥እንሆ፥በዚህ፡ስፍራ፡አመጣለኹ።
4ትተውኛልና፥ይህንም፡ስፍራ፡እንግዳ፡አድርገውታልና፥እነርሱና፡አባቶቻቸውም፡ለማያውቋቸው፡ለሌላዎች፡ አማልክት፡ዐጥነዋልና፥የይሁዳም፡ነገሥታት፡ይህን፡ስፍራ፡በንጹሕ፡ደም፡ሞልተዋልና፥ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
5እኔም፡ያላዘዝኹትን፡ያልተናገርኹትንም፡ወደ፡ልቤም፡ያልገባውን፥የሚቃጠለውን፡መሥዋዕት፡አድርገው፡ ለበዓል፡ልጆቻቸውን፡በእሳት፡ያቃጥሉ፡ዘንድ፡የበዓልን፡የኰረብታውን፡መስገጃዎች፡ሠርተዋልና፥ስለዚህ፥
6እንሆ፥ይህ፡ስፍራ፡የዕርድ፡ሸለቆ፡ይባላል፡እንጂ፡ቶፌት፡ወይም፡የሄኖም፡ልጅ፡ሸለቆ፡ዳግመኛ፡ የማይባልበት፡ዘመን፡ይመጣል፥ይላል፡እግዚአብሔር።
7በዚህም፡ስፍራ፡የይሁዳንና፡የኢየሩሳሌምን፡ምክር፡አፈርሳለኹ፥በጠላቶቻቸውም፡ፊት፡በሰይፍና፡ ነፍሳቸውን፡በሚሹት፡እጅ፡እጥላቸዋለኹ፥ሬሳቸውንም፡ለሰማይ፡ወፎችና፡ለምድር፡አራዊት፡መብል፡አድርጌ፡ እሰጣለኹ።
8ይህችንም፡ከተማ፡ለመደነቂያና፡ለማፏጫ፡አደርጋታለኹ፤የሚያልፍባትም፡ዅሉ፡ስለተደረገባት፡ መቅሠፍት፡ዅሉ፡ይደነቃል፡ከንፈሩንም፡ይመጥጣል።
9የወንዶችና፡የሴቶች፡ልጆቻቸውንም፡ሥጋ፡አበላቸዋለኹ፥ዅሉም፡ጠላቶቻቸውንና፡ነፍሳቸውን፡የሚሹት፡ በሚያስጨንቋቸው፡ጭንቀትና፡መከበብ፡የባልንጀራዎቻቸውን፡ሥጋ፡ይበላሉ።
10ገምቦውንም፡ከአንተ፡ጋራ፡በሚኼዱ፡ሰዎች፡ፊት፡ትሰብራለኽ፥
11እንዲህም፡ትላቸዋለኽ፦የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦የሸክላ፡ሠሪው፡ዕቃ፡ እንደሚሰባበር፡ደግሞም፡ይጠገን፡ዘንድ፡እንደማይቻል፥እንዲሁ፡ይህን፡ሕዝብና፡ይህችን፡ከተማ፡ እሰብራለኹ፤የሚቀብሩበትም፡ስፍራ፡ሌላ፡የለምና፡በቶፌት፡ይቀበራሉ።
12እንዲሁ፡በዚህ፡ስፍራና፡በሚኖሩበት፡ላይ፡አደርጋለኹ፥ይላል፡እግዚአብሔር፥ይህችንም፡ከተማ፡እንደ፡ ቶፌት፡አደርጋለኹ።
13የረከሱትም፡የኢየሩሳሌም፡ቤቶችና፡የይሁዳ፡ነገሥታት፡ቤቶች፥እነዚያ፡በሰገነታቸው፡ላይ፡ለሰማይ፡ ሰራዊት፡ዅሉ፡ያጠኑባቸው፡ለሌላዎችም፡አማልክት፡የመጠጥን፡ቍርባን፡ያፈሰሱባቸው፡ቤቶች፡ዅሉ፥እንደ፡ ቶፌት፡ስፍራ፡ይኾናሉ።
14ኤርምያስም፡እግዚአብሔር፡ትንቢት፡ሊናገር፡ወደዚያ፡ልኮት፡ከነበረው፡ስፍራ፡ከቶፌት፡ መጣ፥በእግዚአብሔርም፡ቤት፡አደባባይ፡ቆሞ፡ለሕዝብ፡ዅሉ፦
15የእስራኤል፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ቃሌን፡እንዳይሰሙ፡ዐንገታቸውን፡ አደንድነዋልና፥እንሆ፥በዚች፡ከተማና፡በመንደሮቿ፡ዅሉ፡ላይ፡የተናገርኹባትን፡ክፉ፡ነገር፡ዅሉ፡ አመጣለኹ።