Skip to content
← Jeremiah

Chapter 24 · Amharic

Jeremiah

1የባቢሎን፡ንጉሥ፡ናቡከደነጾር፡የይሁዳን፡ንጉሥ፡የኢዮአቄምን፡ልጅ፡ኢኮንያንን፡የይሁዳንም፡አለቃዎች፡ ጠራቢዎችንና፡ብረት፡ሠራተኛዎችን፡ከኢየሩሳሌም፡ማርኮ፡ወደ፡ባቢሎን፡ካፈለሳቸው፡በዃላ፥እግዚአብሔር፡ አሳየኝ፥እንሆም፥በእግዚአብሔር፡መቅደስ፡ፊት፡ኹለት፡ቅርጫት፡በለስ፡ተቀምጠው፡ነበር።

2በአንደኛዪቱ፡ቅርጫት፡አስቀድሞ፡እንደ፡ደረሰ፡በለስ፡የሚመስል፡እጅግ፡መልካም፡በለስ፡ ነበረባት፤በኹለተኛዪቱ፡ቅርጫት፡ከክፋቱ፡የተነሣ፡ይበላ፡ዘንድ፡የማይቻል፡እጅግ፡ክፉ፡በለስ፡ነበረባት።

3እግዚአብሔርም፦ኤርምያስ፡ሆይ፥የምታየው፡ምንድር፡ነው፧አለኝ።እኔም፦በለስን፡አያለኹ፤እጅግ፡ መልካም፡የኾነ፡መልካም፡በለስ፥ከክፋቱም፡የተነሣ፡ይበላ፡ዘንድ፡የማይቻል፡እጅግ፡ክፉ፡የኾነ፡ክፉ፡በለስ፡ ነው፡አልኹ።

4የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ወደ፡እኔ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦

5የእስራኤል፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እንደዚህ፡እንደ፡መልካሙ፡በለስ፥እንዲሁ፡ከዚህ፡ ስፍራ፡ወደከለዳውያን፡ምድር፡የሰደድኹትን፡የይሁዳን፡ምርኮ፡ለበጎነት፡እመለከተዋለኹ።

6ዐይኔንም፡ለበጎነት፡በእነርሱ፡ላይ፡አደርጋለኹ፡ወደዚችም፡ምድር፡እመልሳቸዋለኹ፤እሠራቸዋለኹ፡እንጂ፡ አላፈርሳቸውም፤እተክላቸዋለኹ፡እንጂ፡አልነቅላቸውም።

7እኔም፡እግዚአብሔር፡እንደ፡ኾንኹ፡የሚያውቅ፡ልብ፡እሰጣቸዋለኹ፤በፍጹምም፡ልባቸው፡ወደ፡እኔ፡ ይመለሳሉና፡ሕዝብ፡ይኾኑኛል፡እኔም፡አምላክ፡እኾናቸዋለኹ።

8እግዚአብሔርም፡እንዲህ፡ይላል፦ከክፋቱ፡የተነሣ፡ይበላ፡ዘንድ፡እንደማይቻል፡እንደ፡ክፉው፡ በለስ፥እንዲሁ፡የይሁዳን፡ንጉሥ፡ሴዴቅያስን፡አለቃዎቹንም፡በዚችም፡አገር፡የሚቀሩትን፡የኢየሩሳሌም፡ቅሬታ፡ በግብጽም፡አገር፡የሚቀመጡትን፡እጥላቸዋለኹ።

9በማሳድዳቸውም፡ስፍራ፡ዅሉ፡ለስድብና፡ለምሳሌ፡ለማላገጫና፡ለርግማን፡ይኾኑ፡ዘንድ፡በምድር፡ መንግሥታት፡ዅሉ፡ለመበተን፡አሳልፌ፡እሰጣቸዋለኹ።

10ለእነርሱና፡ለአባቶቻቸውም፡ከሰጠዃቸው፡ምድር፡እስኪጠፉ፡ድረስ፡በመካከላቸው፡ሰይፍንና፡ራብን፡ ቸነፈርንም፡እሰዳ፟ለኹ።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source