1በሰው፡ዘንድ፦ሰው፡ሚስቱን፡ቢፈታ፥ከርሱም፡ዘንድ፡ኼዳ፡ሌላ፡ወንድ፡ብታገባ፥በእውኑ፡ደግሞ፡ወደ፡ ርሱ፡ትመለሳለችን፧ያች፡ሴት፡እጅግ፡የረከሰች፡አይደለችምን፧ይባላል።አንቺ፡ከብዙ፡ውሽማዎች፡ጋራ፡ አመንዝረሻል፥ወደ፡እኔም፡ትመለሻለሽን፧ይላል፡እግዚአብሔር።
2ዐይንሽን፡አንሥተሽ፡ወደ፡ወናዎች፡ኰረብታዎች፡ተመልከቺ፤ያልተጋደምሽበት፡ስፍራ፡ወዴት፡ አለ፧ዐረባዊ፡በምድረ፡በዳ፡እንደሚቀመጥ፡አንቺ፡በመንገድ፡ላይ፡ተቀምጠሽ፡ትጠብቂያቸው፡ ነበር፤በግልሙትናሽና፡በኀጢአትሽ፡ምድሪቱን፡አረከ፟ሽ።
3ስለዚህ፥ካፊያ፡ተከለከለ፥የዃለኛውም፡ዝናብ፡ጠፋ፤የጋለሞታም፡ሴት፡ፊት፡ነበረብሽ፥ታፍሪም፡ዘንድ፡ እንቢ፡ብለሻል።
4አኹንም፦አንተ፡አባቴ፡ሆይ፥የብላቴንነቴ፡ወዳጅ፡ነኽ፡ብለሽ፡አልጮኽሺልኝምን፧ለዘለዓለም፡ ይቈጣልን፧
5እስከ፡ፍጻሜስ፡ድረስ፡ይጠብቀዋልን፧እንሆ፥እንዲህ፡ብለሽ፡ተናገርሽ፥እንደ፡ተቻለሽም፡መጠን፡ክፉን፡ ነገር፡አደረግሽ።
6እግዚአብሔርም፡በንጉሡ፡በኢዮስያስ፡ዘመን፡እንዲህ፡አለኝ፦ከዳ፟ተኛዪቱ፡እስራኤል፡ያደረገችውን፡ አየኽን፧ወደረዘመው፡ተራራ፡ዅሉ፡ከለመለመ፡ዛፍም፡ዅሉ፡በታች፡ኼደች፡በዚያም፡ጋለሞተች።
7ይህንም፡ዅሉ፡ካደረገች፡በዃላ፦ወደ፡እኔ፡ትመለሳለች፡ብዬ፡ነበር፤ነገር፡ ግን፥አልተመለሰችም፤አታላይ፡እኅቷም፡ይሁዳ፡አየች።
8ከዳ፟ተኛዪቱም፡እስራኤል፡ስላመነዘረች፡ስለዚህ፡ፈትቻታለኹ፡የፍቿንም፡ወረቀት፡ሰጥቻታለኹ፤አታላይ፡ እኅቷ፡ይሁዳ፡ግን፡እንዳልፈራች፡ርሷም፡ደግሞ፡ኼዳ፡እንደ፡ጋለሞተች፡አየኹ።
9በግልሙትናዋም፡በመቅለሏም፡ምድሪቱ፡ረከሰች፤ርሷም፡ከድንጋይና፡ከግንድ፡ጋራ፡አመነዘረች።
10በዚህም፡ዅሉ፡አታላዪቱ፡ይሁዳ፡በሐሰት፡እንጂ፡በፍጹም፡ልቧ፡ወደ፡እኔ፡አልተመለሰችም።
11እግዚአብሔርም፡እንዲህ፡አለኝ፦ከአታላዪቱ፡ከይሁዳ፡ይልቅ፡ከዳ፟ተኛዪቱ፡እስራኤል፡ጸደቀች።
12ኺድና፡ይህን፡ቃል፡ወደ፡ሰሜን፡ተናገር፥እንዲህም፡በል፦ከዳ፟ተኛዪቱ፡እስራኤል፡ ሆይ፥ተመለሽ፥ይላል፡እግዚአብሔር፤መሓሪ፡ነኝና፥ለዘለዓለምም፡አልቈጣምና፡በእናንተ፡ላይ፡ፊቴን፡ አላደርግም፥ይላል፡እግዚአብሔር።
13በአምላክሽ፡በእግዚአብሔር፡ላይ፡እንዳመፅሽ፥መንገድሽንም፡ከለመለመ፡ዛፍ፡ዅሉ፡በታች፡ለእንግዳዎች፡ እንደ፡ዘረጋሽ፥ቃሌንም፡እንዳልሰማሽ፡ኀጢአትሽን፡ብቻ፡ዕወቂ፡ይላል፡እግዚአብሔር።
14ከዳ፟ተኛዎች፡ልጆች፡ሆይ፥እኔ፡ባላችኹ፡ነኝና፡ተመለሱ፡ይላል፡እግዚአብሔር፤አንዱንም፡ከአንዲት፡ ከተማ፡ኹለቱንም፡ካንድ፡ወገን፡እወስዳችዃለኹ፥ወደ፡ጽዮንም፡አመጣችዃለኹ፤
15እንደ፡ልቤም፡በግ፡ጠባቂዎችን፡እሰጣችዃለኹ፥በዕውቀትና፡በማስተዋልም፡ይጠብቋችዃል።
16በበዛችኹም፡ጊዜ፡በምድርም፡ላይ፡በረባችኹ፡ጊዜ፥ይላል፡እግዚአብሔር፥በዚያ፡ ዘመን፦የእግዚአብሔር፡የቃል፡ኪዳኑ፡ታቦት፡ብለው፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡አይጠሩም፤ልብ፡ አያደርጉትም፥አያስቡትምም፥አይሹትምም፥ከእንግዲህ፡ወዲህም፡አይደረግም።
17በዚያም፡ዘመን፡ኢየሩሳሌምን፡የእግዚአብሔር፡ዙፋን፡ብለው፡ይጠሯታል፥አሕዛብም፡ዅሉ፡ወደ፡ርሷ፡ ይሰበሰባሉ፤ከእንግዲህም፡ወዲህ፡ክፉውን፡እልከኛ፡ልባቸውን፡ተከትለው፡አይኼዱም።
18በዚያም፡ዘመን፡የይሁዳ፡ቤት፡ወደእስራኤል፡ቤት፡ይኼዳል፤በአንድም፡ኾነው፡ከሰሜን፡ምድር፡ርስት፡ አድርጌ፡ለአባቶቻቸው፡ወደሰጠዃት፡ምድር፡ይመጣሉ።
19እኔ፡ግን፦ከወንዶች፡ልጆች፡ጋራ፡እንዴት፡አደርግሻለኹ፧ያማረችውንስ፡ምድር፡የከበረችውን፡ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org የአሕዛብን፡ሰራዊት፡ርስት፡እንዴት፡እሰጥሻለኹ፧ብዬ፡ነበር።ደግሞ፦አባቴ፡ብለሽ፡ትጠሪኛለሽ፥እኔንም፡ ከመከተል፡አትመለሽም፡ብዬ፡ነበር።
20የእስራኤል፡ቤት፡ሆይ፥ሚስት፡ባሏን፡እንደምታታልል፡እንዲሁ፡አታለላችኹኝ፡ይላል፡እግዚአብሔር።
21የእስራኤል፡ልጆች፡መንገዳቸውን፡አጣ፟መ፟ዋልና፥አምላካቸውንም፡እግዚአብሔርን፡ረስተዋልና፥በወናዎች፡ ኰረብታዎች፡ላይ፡የልመናቸውና፡ልቅሷቸው፡ድምፅ፡ተሰማ።
22ከዳ፟ተኛዎች፡ልጆች፡ሆይ፥ተመለሱ፥ከዳ፟ተኛነታችኹንም፡እፈውሳለኹ።እንሆ፥አንተ፡አምላካችን፡ እግዚአብሔር፡ነኽና፥ወዳንተ፡እንመጣለን።
23በእውነት፡የኰረብታዎችና፡የተራራዎች፡ፍጅት፡ከንቱ፡ናት፤በእውነት፡የእስራኤል፡መዳን፡በአምላካችን፡ በእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ነው።
24ነገር፡ግን፥ከትንሽነታችን፡ዠምሮ፡የአባቶቻችን፡ድካም፥በጎቻቸውንና፡ላሞቻቸውን፡ወንዶችና፡ሴቶች፡ ልጆቻቸውንም፥ዕፍረት፡በልቶባቸዋል።
25ከትንሽነታችን፡ዠምሮ፡እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡እኛና፡አባቶቻችን፡በአምላካችን፡በእግዚአብሔር፡ላይ፡ ኀጢአት፡ሠርተናልና፥የአምላካችንንም፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡አልሰማንምና፡በዕፍረታችን፡ እንጋደም፥ውርደታችንም፡ይክደነን።