1እስራኤል፡ሆይ፥ብትመለስ፥ወደ፡እኔ፡ተመለስ፥ይላል፡እግዚአብሔር፤ርኵሰትኽንም፡ከፊቴ፡ ብታስወግድ፥ባትናወጥም፥
2ሕያው፡እግዚአብሔርን! ብለኽም፡በእውነትና፡በቅንነት፡በጽድቅም፡ብትምል፥አሕዛብ፡በርሱ፡ይባረካሉ፡ በርሱም፡ይመካሉ።
3እግዚአብሔር፡ለይሁዳና፡ለኢየሩሳሌም፡ሰዎች፡እንዲህ፡ይላልና፦ጥጋቱን፡ዕርሻ፡ዕረሱ፥በሾኽም፡ላይ፡ አትዝሩ።
4እናንተም፡የይሁዳ፡ሰዎች፡በኢየሩሳሌምም፡የምትኖሩ፡ሆይ፥ስለሥራችኹ፡ክፋት፡ቍጣዬ፡እንደ፡እሳት፡ እንዳይወጣ፡የሚያጠፋውም፡ሳይኖር፡እንዳያቃጥል፥ለእግዚአብሔር፡ተገረዙ፥የልባችኹንም፡ሸለፈት፡አስወግዱ።
5በይሁዳ፡ዘንድ፡ተናገሩ፥በኢየሩሳሌምም፡ላይ፡አውሩና፦በአገሪቱ፡ላይ፡መለከት፡ንፉ፡ በሉ፤ጮኻችኹም፦ዅላችኹ፡ተሰብሰቡ፡ወደተመሸጉትም፡ከተማዎች፡እንግባ፡በሉ።
6ከሰሜን፡ክፉ፡ነገርንና፡ጽኑ፡ጥፋትን፡አመጣለኹና፡ወደ፡ጽዮን፡ዐላማን፡አንሡ፤ሽሹ፥አትዘግዩ።
7አንበሳ፡ከጭፍቅ፡ዱር፡ወጥቷል፥አሕዛብንም፡የሚዘርፍ፡ተነሥቷል፤ምድርሽን፡ባድማ፡ያደርግ፡ዘንድ፡ ከስፍራው፡ወጥቷል፥ከተማዎችሽም፡ሰው፡የሌለባቸው፡ፍርስራሾች፡ይኾናሉ።
8የእግዚአብሔር፡ጽኑ፡ቍጣ፡ከእኛ፡ዘንድ፡አልተመለሰምና፡ማቅ፡ልበሱ፥አልቅሱም፡ዋይም፡በሉ።
9በዚያም፡ቀን፥ይላል፡እግዚአብሔር፥የንጉሡና፡የመኳንንቱ፡ልብ፡ይጠፋል፥ካህናቱም፡ይደነቃሉ፡ ነቢያቱም፡ይደነግጣሉ።
10እኔም፦ጌታ፡እግዚአብሔር፡ሆይ፥ወዮ፥አንተ፡ሰይፍ፡እስከ፡ነፍስ፡ድረስ፡በደረሰ፡ጊዜ፦ሰላም፡ ይኾንላችዃል፡ብለኽ፡ይህን፡ሕዝብና፡ኢየሩሳሌምን፡እጅግ፡አታለልኽ፡አልኹ።
11በዚያ፡ጊዜ፡ለዚህ፡ሕዝብና፡ለኢየሩሳሌም፦ለማበጠር፡ወይም፡ለማጥራት፡ሳይኾን፡የሚያቃጥል፡ነፋስ፡ በምድረ፡በዳ፡ካሉ፡ከወናዎች፡ኰረብታዎች፡ወደወገኔ፡ሴት፡ልጅ፡ይመጣል፤
12ስለ፡እኔ፡ጽኑ፡የኾነ፡ነፋስ፡ከነዚህ፡ይመጣል፡ይባላል።አኹንም፡እኔ፡ደግሞ፡ፍርዴን፡በእነርሱ፡ላይ፡ እናገራለኹ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
13እንሆ፥እንደ፡ደመና፡ይወጣል፥ሠረገላዎቹም፡እንደ፡ዐውሎ፡ነፋስ፤ፈረሶቹም፡ከንስር፡ይልቅ፡ፈጣኖች፡ ናቸው።ጠፍተናልና፥ወዮልን።
14ኢየሩሳሌም፡ሆይ፥ትድኚ፡ዘንድ፡ልብሽን፡ከክፉ፡ነገር፡ዕጠቢ።ክፉ፡ዐሳብ፡የሚኖርብሽ፡እስከ፡መቼ፡ ድረስ፡ነው፧
15የተናጋሪ፡ድምፅ፡ከዳን፡ዘንድ፡ይናገራልና፥ከኤፍሬምም፡ኰረብታዎች፡መከራን፡ያወራልና።
16ለአሕዛብ፡አሰሙና፦እንሆ፥ጠባቂዎች፡ከሩቅ፡አገር፡ይመጣሉ፤በይሁዳም፡ከተማዎች፡ላይ፡ይጮኻሉ፡ ብላችኹ፡በኢየሩሳሌም፡ላይ፡አውሩ።
17በእኔ፡ላይ፡ዐመፀኛ፡ኾናለችና፡በዙሪያዋ፡ከበ፟ው፡እንደ፡ዕርሻ፡ጠባቂዎች፡ኾነውባታል፥ይላል፡ እግዚአብሔር።
18መንገድሽና፡ሥራሽ፡ይህን፡አድርጎብሻል፤ይህ፡ክፋትሽ፡መራር፡ነው፥ወደ፡ልብሽም፡ደርሷል።
19አንዠቴ! አንዠቴ! ልቤ፡በጣም፡ታሟ፟ል፥በውስጤም፡ልቤ፡ታውኮብኛል፤ነፍሴ፡ሆይ፥የመለከትን፡ ድምፅና፡የሰልፍን፡ውካታ፡ሰምተሻልና፥ዝም፡እል፡ዘንድ፡አልችልም።
20መከራ፡በመከራ፡ላይ፡ተጠርቷል፤ምድርም፡ዅሉ፡ተበዝብዛለችና፤በድንገትም፡ድንኳኔ፡በቅጽበት፡ ዐይንም፡መጋረጃዎቼ፡ጠፉ።
21ዐላማውን፡የምመለከት፥የመለከቱንስ፡ድምፅ፡የምሰማ፡እስከ፡መቼ፡ነው፧
22ሕዝቤ፡ሰንፈዋልና፥አላወቁኝም፤ሰነፎች፡ልጆች፡ናቸው፥ማስተዋልም፡የላቸውም፤ክፉ፡ነገርን፡ ለማድረግ፡ብልኀተኛዎች፡ናቸው፥በጎ፡ነገርን፡ማድረግ፡ግን፡አያውቁም።
23ምድሪቱን፡አየኹ፥እንሆም፥ባዶ፡ነበረች፡አንዳችም፡አልነበረባትም፤ሰማያትንም፡አየኹ፥ብርሃንም፡ አልነበረባቸውም።
24ተራራዎችን፡አየኹ፥እንሆም፥ተንቀጠቀጡ፥ኰረብታዎችም፡ዅሉ፡ተናወጡ።
25አየኹ፥እንሆም፥ሰው፡አልነበረም፥የሰማይም፡ወፎች፡ዅሉ፡ሸሽተው፡ነበር።
26አየኹ፥እንሆም፥ፍሬያማ፡ዕርሻ፡ምድረ፡በዳ፡ኾነች፥ከተማዎችም፡ዅሉ፡ከእግዚአብሔር፡ፊት፡ከጽኑ፡ ቍጣው፡የተነሣ፡ፈርሰው፡ነበር።
27እግዚአብሔርም፡እንዲህ፡ይላል፦ምድር፡ዅሉ፡ባድማ፟፡ትኾናለች፥ነገር፡ግን፥ፈጽሜ፡አላጠፋትም።
28ስለዚህ፥ምድር፡ታለቅሳለች፥በላይም፡ሰማይ፡ይጠቍራል፤ተናግሬያለኹና፥ዐስቤያለኹም፤አልጸጸትም፡ ከርሱም፡አልመለስም።
29ከፈረሰኛዎችና፡ከቀስተኛዎች፡ድምፅ፡የተነሣ፡ከተማ፡ዅሉ፡ሸሽታለች፤ወደችፍግ፡ዱርም፡ይገባሉ፡ በቋጥኝ፡ላይም፡ይወጣሉ፤ከተማ፡ዅሉ፡ተለቃ፟ለች፡የሚቀመጥባትም፡ሰው፡የለም።
30አንቺም፡የተበዘበዝሽ፡ሆይ፥ምን፡ታደርጊያለሽ፧ቀይ፡በለበስሽ፡ጊዜ፥በወርቅ፡አንባርም፡ባጌጥሽ፡ ጊዜ፥ዐይንሽንም፡በኵል፡በተኳልሽ፡ጊዜ፥በከንቱ፡ታጌጫለሽ፤ውሽማዎችሽ፡አቃለሉሽ፥ነፍስሽን፡ይሿታል።
31እንደምታምጥ፡የበኵሯንም፡እንደምትወልድ፡ሴት፡ድምፅ፡ሰምቻለኹና፤የጽዮን፡ሴት፡ልጅ፡ድምፅ፡ በድካም፡ይሰልላል፥እጆቿንም፡ትዘረጋለችና፦ተገድለው፡ከሞቱት፡የተነሣ፡ነፍሴ፡ዝላለችና፡ወዮልኝ! አለች።