Skip to content
← Jeremiah

Chapter 33 · Amharic

Jeremiah

1ኤርምያስ፡ገና፡በግዞት፡ቤት፡አደባባይ፡ታስሮ፡ሳለ፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡ኹለተኛ፡ጊዜ፡እንዲህ፡ሲል፡ መጣለት፦

2ስሙ፡እግዚአብሔር፡የኾነ፥ያደረገው፡እግዚአብሔር፥ያጸናውም፡ዘንድ፡የሠራው፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ ይላል፦

3ወደ፡እኔ፡ጩኽ፥እኔም፡እመልስልኻለኹ፤አንተም፡የማታውቀውን፡ታላቅና፡ኀይለኛ፡ነገርን፡አሳይኻለኹ።

4የእስራኤል፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡ለዐፈር፡ድልድልና፡ለምሽግ፡ስለ፡ፈረሱ፡ስለዚች፡ከተማ፡ ቤቶች፥ስለይሁዳም፡ነገሥታት፡ቤቶች፡እንዲህ፡ይላልና፦

5ከለዳውያን፡ለመዋጋት፡መጥተዋል፤ነገር፡ግን፥በቍጣዬና፡በመዓቴ፡በገደልዃቸው፡ሰዎች፡ሬሳዎች፡ ሊሞሏቸው፡ነው፥ስለ፡ክፋታቸው፡ዅሉ፡ፊቴን፡ከዚች፡ከተማ፡ሰውሬያለኹና።

6እንሆ፥ፈውስንና፡መድኀኒትን፡አመጣላታለኹ፥እፈውሳቸውማለኹ፤የሰላምንና፡የእውነትን፡ብዛት፡ እገልጥላቸዋለኹ።

7የይሁዳን፡ምርኮና፡የእስራኤልንም፡ምርኮ፡እመልሳለኹ፥ቀድሞም፡እንደ፡ነበሩ፡አድርጌ፡እሠራቸዋለኹ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

8እኔንም፡ከበደሉበት፡ኀጢአት፡ዅሉ፡አነጻቸዋለኹ፡እኔንም፡የበደሉኝን፡ያመፀብኝንም፡ኀጢአታቸውን፡ዅሉ፡ ይቅር፡እላለኹ።

9ይህችም፡ከተማ፡እኔ፡የምሠራላቸውን፡በጎነት፡ዅሉ፡በሚሰሙ፡እኔም፡ስላመጣኹላቸው፡በጎነትና፡ሰላም፡ ዅሉ፡በሚፈሩና፡በሚደነግጡ፡አሕዛብ፡ዅሉ፡ፊት፡ለደስታ፡ስም፡ለምስጋናም፡ለክብርም፡ትኾናለች።

10እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እናንተ፦ያለሰውና፡ያለእንስሳ፡ያለች፡ባድማ፡ናት፡በምትሏት፡በዚች፡ ስፍራ፥የሚቀመጥባቸው፡በሌላ፥ያለሰውና፡ያለእንስሳ፡ባድማ፡በኾኑ፡በይሁዳ፡ከተማዎችና፡በኢየሩሳሌም፡ አደባባይ፥

11የሐሤት፡ድምፅና፡የደስታ፡ድምፅ፥የወንድ፡ሙሽራ፡ድምፅና፡የሴት፡ሙሽራ፡ድምፅ፦እግዚአብሔር፡ ቸር፡ነውና፥ምሕረቱም፡ለዘለዓለም፡ነውና፥የሰራዊትን፡ጌታ፡እግዚአብሔርን፡አመስግኑ፡የሚሉ፡ ድምፅ፥ወደእግዚአብሔርም፡ቤት፡የምስጋናን፡መሥዋዕት፡የሚያመጡት፡ድምፅ፡እንደ፡ገና፡ ይሰማል።የምድርን፡ምርኮ፡ቀድሞ፡እንደ፡ነበረ፡አድርጌ፡እመልሳለኹና፥ይላል፡እግዚአብሔር።

12የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ባድማ፡ኾኖ፥ያለሰውና፡ያለእንስሳ፡ባለው፡በዚህ፡ስፍራ፡ በከተማዎችም፡ዅሉ፡መንጋዎቻቸውን፡የሚያሳርፉት፡የእረኛዎች፡መኖሪያ፡ይኾናል።

13በደጋው፡ላይ፡ባሉ፡ከተማዎች፡በቈላውም፡ባሉ፡ከተማዎች፡በደቡብም፡ባሉ፡ከተማዎች፥በብንያምም፡ አገር፡በኢየሩሳሌምም፡ዙሪያ፡ባሉ፡ስፍራዎች፥በይሁዳም፡ከተማዎች፡መንጋዎቹ፡በተቈጣጣሪው፡እጅ፡እንደ፡ ገና፡ያልፋሉ፥ይላል፡እግዚአብሔር።

14እንሆ፥ስለእስራኤል፡ቤትና፡ስለይሁዳ፡ቤት፡የተናገርኹትን፡መልካም፡ቃል፡የምፈጽምበት፡ዘመን፡ ይመጣል፥ይላል፡እግዚአብሔር።

15በዚያም፡ዘመን፡በዚያም፡ጊዜ፡ለዳዊት፡የጽድቅን፡ቍጥቋጥ፡አበቅልለታለኹ፤ርሱም፡ፍርድንና፡ጽድቅን፡ በምድር፡ያደርጋል።

16በዚያም፡ዘመን፡ይሁዳ፡ይድናል፡ኢየሩሳሌምም፡ተዘልላ፡ትቀመጣለች፤የምትጠራበትም፡ ስም፦እግዚአብሔር፡ጽድቃችን፡ተብሎ፡ነው።

17እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላልና፦በእስራኤል፡ቤት፡ዙፋን፡ላይ፡የሚቀመጥ፡ሰው፡ከዳዊት፡ዘንድ፡ አይታጣም፤

18የሚቃጠለውንም፡መሥዋዕት፡የሚያቀርብ፡የእኽሉንም፡ቍርባን፡የሚያቃጥል፡ዅልጊዜም፡የሚሠዋ፡ሰው፡ ከሌዋውያን፡ካህናት፡ዘንድ፡በእኔ፡ፊት፡አይታጣም።

19የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ወደ፡ኤርምያስ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦

20እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ቀንና፡ሌሊት፡በወራቱ፡እንዳይኾን፡የቀን፡ቃል፡ኪዳኔንና፡የሌሊት፡ቃል፡ ኪዳኔን፡ማፍረስ፡ብትችሉ፥

21በዙፋኑ፡ላይ፡የሚነግሥ፡ልጅ፡እንዳይኾንለት፡ከባሪያዬ፡ከዳዊት፡ጋራ፥ከአገልጋዮቼም፡ከሌዋውያን፡ ካህናት፡ጋራ፡ያለው፡ቃል፡ኪዳኔ፡ደግሞ፡ይፈርሳል።

22የሰማይን፡ሰራዊት፡መቍጠር፡የባሕርንም፡አሸዋ፡መስፈር፡እንደማይቻል፥እንዲሁ፡የባሪያዬን፡የዳዊትን፡ ዘርና፡የሚያገለግሉኝን፡ሌዋውያንን፡አበዛለኹ።

23የእግዚአብሔር፡ቃል፡ወደ፡ኤርምያስ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦

24ይህ፡ሕዝብ፦እግዚአብሔር፡የመረጣቸውን፡ኹለቱን፡ወገን፡ጥሏቸዋል፡ያለውን፡ነገር፡ አትመለከትምን፧እንዲሁ፡በፊታቸው፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡ሕዝብ፡እንዳይኾን፡ሕዝቤን፡አቃለ፟ዋል።

25እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦የቀንና፡የሌሊት፡ቃል፡ኪዳኔን፡የሰማይንና፡የምድርንም፡ሥርዐት፡ ያላጸናኹ፡እንደ፡ኾነ፥ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

26እኔም፡ደግሞ፡በአብርሃምና፡በይሥሐቅ፡በያዕቆብም፡ዘር፡ላይ፡ገዢዎች፡ይኾኑ፡ዘንድ፡ከዘሩ፡ እንዳልወስድ፥የያዕቆብንና፡የባሪያዬን፡የዳዊትን፡ዘር፡እጥላለኹ፤ምርኳቸውን፡ እመልሳለኹና፥እምራቸውማለኹና።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source