Skip to content
← Jeremiah

Chapter 35 · Amharic

Jeremiah

1በይሁዳ፡ንጉሥ፡በኢዮስያስ፡ልጅ፡በኢዮአቄም፡ዘመን፡ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ወደ፡ኤርምያስ፡የመጣ፡ ቃል፡ይህ፡ነው፦

2ወደሬካባውያን፡ቤት፡ኼደኽ፡ተናገራቸው፥ወደእግዚአብሔርም፡ቤት፡ከጓዳዎቹ፡ወደ፡አንዲቱ፡አግባቸው፡ የወይን፡ጠጅም፡አጠጣቸው።

3የከባስንን፡ልጅ፡የኤርምያስን፡ልጅ፡ያእዛንያን፡ወንድሞቹንም፡ልጆቹንም፡ዅሉ፡የሬካባውያንን፡ወገን፡ ዅሉ፡ወሰድዃቸው፤

4ወደእግዚአብሔርም፡ቤት፡በበረኛው፡በሰሎም፡ልጅ፡በመዕሴያ፡ጓዳ፡በላይ፡ባለው፡በአለቃዎች፡ጓዳ፡ አጠገብ፡ወዳለው፡ወደእግዚአብሔር፡ሰው፡ወደጌዴልያ፡ልጅ፡ወደሐናን፡ልጆች፡ጓዳ፡አገባዃቸው።

5በሬካባውያንም፡ልጆች፡ፊት፡የወይን፡ጠጅ፡የሞላባቸውን፡ማድጋዎችንና፡ጽዋዎችን፡አኑሬ፦የወይኑን፡ ጠጅ፡ጠጡ፡አልዃቸው።

6እነርሱ፡ግን፡እንዲህ፡አሉ፦የወይኑን፡ጠጅ፡አንጠጣም፥አባታችን፡የሬካብ፡ልጅ፡ኢዮናዳብ፡እንዲህ፡ ብሎ፡አዞ፟ናልና።እናንተና፡ልጆቻችኹ፡ለዘለዓለም፡የወይን፡ጠጅ፡አትጠጡ።

7በምትኖሩባት፡ምድር፡ላይ፡ብዙ፡ዘመን፡እንድትኖሩ፥በዕድሜያችኹ፡ሙሉ፡በድንኳን፡ውስጥ፡ተቀመጡ፡ እንጂ፡ቤትን፡አትሥሩ፥ዘርንም፡አትዝሩ፥ወይንም፡አትትከሉ፥አንዳችም፡አይኹንላችኹ።

8እኛም፡የአባታችንን፡የሬካብ፡ልጅ፡የኢዮናዳብን፡ቃል፡ባዘዘን፡ነገር፡ዅሉ፡ታዘ፟ናል፤እኛም፡ ሚስቶቻችንም፡ወንዶችና፡ሴቶች፡ልጆቻችንም፡ዕድሜያችንን፡ሙሉ፡የወይን፡ጠጅ፡አልጠጣንም፤

9የምንቀመጥበትንም፡ቤት፡አልሠራንም፤የወይን፡ቦታና፡ዕርሻ፡ዘርም፡የለንም፤

10በድንኳንም፡ውስጥ፡ተቀምጠናል፥ታዘ፟ናል፥አባታችንም፡ኢዮናዳብ፡ያዘዘንን፡ዅሉ፡አድርገናል።

11ነገር፡ግን፥የባቢሎን፡ንጉሥ፡ናቡከደነጾር፡ወደዚች፡ምድር፡በመጣ፡ጊዜ፦ኑ፡ከከለዳውያን፡ሰራዊትና፡ ከሶርያ፡ሰራዊት፡ፊት፡የተነሣ፡ወደ፡ኢየሩሳሌም፡እንኺድ፡አልን፤እንዲሁም፡በኢየሩሳሌም፡ተቀመጥን።

12የእግዚአብሔርም፡ቃል፡ወደ፡ኤርምያስ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

13የእስራኤል፡አምላክ፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ኺድና፡ለይሁዳ፡ሰዎችና፡ በኢየሩሳሌም፡ለሚቀመጡ፡ተናገር፡እንዲህም፡በላቸው፦ቃሌን፡ትሰሙ፡ዘንድ፡ተግሣጽን፡ አትቀበሉምን፧ይላል፡እግዚአብሔር።

14የሬካብ፡ልጅ፡ኢዮናዳብ፡ልጆቹ፡የወይን፡ጠጅ፡እንዳይጠጡ፡ያዘዛቸው፡ቃል፡ተፈጸመ፤ለአባታቸውም፡ ትእዛዝ፡ታዘ፟ዋልና፥እስከ፡ዛሬ፡ድረስ፡አይጠጡም፤እኔም፡በማለዳ፡ተነሥቼ፡ ተናግሬያችዃለኹ፤ተናገርኹ፥ኾኖም፡አልሰማችኹኝም።

15ደግሞም፦እያንዳንዳችኹ፡ከክፉ፡መንገዳችኹ፡ተመለሱ፥ሥራችኹንም፡አሳምሩ፥ታመልኳቸውም፡ዘንድ፡ ሌላዎችን፡አማልክት፡አትከተሉ፥ለእናንተና፡ለአባቶቻችኹም፡በሰጠኹት፡ምድር፡ትቀመጣላችኹ፡እያልኹ፡ በማለዳ፡ተነሥቼ፡ባሪያዎቼን፡ነቢያትን፡ዅሉ፡ልኬባችኹ፡ነበር፤እናንተ፡ግን፡ዦሯችኹን፡አላዘነበላችኹም፡ እኔንም፡አልሰማችኹኝም።

16የሬካብ፡ልጅ፡የኢዮናዳብ፡ልጆች፡አባታቸው፡ያዘዛቸውን፡ትእዛዝ፡ፈጽመዋልና፥ይህ፡ሕዝብ፡ግን፡ አልሰማኝምና፤

17ስለዚህ፥የእስራኤል፡አምላክ፣የሰራዊት፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እንሆ፥በተናገርዃቸው፡ ጊዜ፡አልሰሙምና፥በጠራዃቸውም፡ጊዜ፡አልመለሱልኝምና፡የተናገርኹባቸውን፡ክፉ፡ነገር፡ዅሉ፡በይሁዳ፡ ላይ፡በኢየሩሳሌምም፡በሚቀመጡ፡ዅሉ፡ላይ፡አመጣባቸዋለኹ።

18ኤርምያስም፡ሬካባውያንን፡እንዲህ፡አላቸው፦የእስራኤል፡አምላክ፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ ይላል፦ለአባታችኹ፡ለኢዮናዳብ፡ትእዛዝ፡ታዛ፟ችዃልና፥ትእዛዙንም፡ዅሉ፡ጠብቃችዃልና፥ያዘዛችኹንም፡ ፈጽማችዃልና፤

19ስለዚህ፥በፊቴ፡የሚቆም፡ሰው፡ከሬካብ፡ልጅ፡ከኢዮናዳብ፡ወገን፡ለዘለዓለም፡አይታጣም።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source