1ኤርምያስም፡ለሕዝቡ፡ዅሉ፡የተናገረውን፡ቃል፡የማታን፡ልጅ፡ስፋጥያስ፥የጳስኮርም፡ልጅ፡ ጎዶልያስ፥የሰሌምያም፡ልጅ፡ዮካል፥የመልክያም፡ልጅ፡ጳስኮር፡ሰሙ።
2ኤርምያስ፡እንዲህ፡ብሏልና፦እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በዚች፡ከተማ፡የሚቀመጥ፡በሰይፍና፡በራብ፡ በቸነፈርም፡ይሞታል፤ወደ፡ከለዳውያን፡ግን፡የሚወጣ፡በሕይወት፡ይኖራል፥ነፍሱም፡እንደ፡ምርኮ፡ ትኾንለታለች፥በሕይወትም፡ይኖራል።
3እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላልና፦ይህች፡ከተማ፡በባቢሎን፡ንጉሥ፡ሰራዊት፡እጅ፡በርግጥ፡ ትሰጣለች፥ርሱም፡ይይዛታል።
4አለቃዎቹም፡ንጉሡን፦ይህን፡የመሰለውን፡ቃል፡ሲነግራቸው፡በዚች፡ከተማ፡የቀሩትን፡የሰልፈኛዎቹን፡ እጅ፡የሕዝቡንም፡ዅሉ፡እጅ፡ያደክማልና፥ይህ፡ሰው፡እንዲገደል፡እንለምንኻለን፤ይህ፡ሰው፡ክፋትን፡እንጂ፡ ለዚህ፡ሕዝብ፡ሰላምን፡አይመኝለትምና፡አሉት።
5ንጉሡም፡ሴዴቅያስ፦ንጉሡ፡በእናንተ፡ላይ፡ምንም፡ሊያደርግ፡አይችልምና፥እንሆ፥በእጃችኹ፡ነው፡ አለ።
6ኤርምያስንም፡ወሰዱት፡በግዞት፡ቤቱም፡አደባባይ፡ወደነበረው፡ወደንጉሡ፡ልጅ፡ወደመልክያ፡ጕድጓድ፡ ውስጥ፡ጣሉት፤ኤርምያስንም፡በገመድ፡አወረዱት።በጕድጓድም፡ውስጥ፡ጭቃ፡እንጂ፡ውሃ፡ አልነበረበትም፤ኤርምያስም፡ወደ፡ጭቃው፡ውስጥ፡ገባ።
7በንጉሡም፡ቤት፡የነበረው፡ጃን፡ደረባ፡ኢትዮጵያዊው፡አቢሜሌክ፡ኤርምያስን፡በጕድጓዱ፡ውስጥ፡ እንዳኖሩት፡ሰማ።ንጉሡም፡በብንያም፡በር፡ተቀምጦ፡ነበር።
8አቢሜሌክም፡ከንጉሡ፡ቤት፡ወጥቶ፡ንጉሡን፡እንዲህ፡አለው፦
9ጌታዬ፡ንጉሥ፡ሆይ፥እነዚህ፡ሰዎች፡ነቢዩን፡ኤርምያስን፡በጕድጓድ፡ውስጥ፡በመጣላቸው፡በርሱ፡ላይ፡ በማድረጋቸው፡ዅሉ፡ክፉ፡አድርገዋል፤በከተማዪቱም፡ውስጥ፡እንጀራ፡ስለሌለ፡በዚያ፡በራብ፡ይሞታል።
10ንጉሡም፡ኢትዮጵያዊውን፡አቢሜሌክም፦ከአንተ፡ጋራ፡ሠላሳ፡ሰዎች፡ከዚህ፡ውሰድ፥ነቢዩም፡ኤርምያስ፡ ሳይሞት፡ከጕድጓድ፡አውጣው፡ብሎ፡አዘዘው።
11አቢሜሌክም፡ከርሱ፡ጋራ፡ሰዎችን፡ይዞ፡ኼደ፥ከቤተ፡መዛግብቱም፡በታች፡ወደነበረው፡ወደንጉሥ፡ቤት፡ ገባ፥ከዚያም፡አሮጌ፡ጨርቅና፡ዕላቂ፡ልብስ፡ወሰደ፥ወደ፡ኤርምያስም፡ወደ፡ጕድጓድ፡ውስጥ፡በገመድ፡ አወረደው። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
12ኢትዮጵያዊውም፡አቢሜሌክ፡ኤርምያስን፦ይህን፡አሮጌ፡ጨርቅና፡ዕላቂውን፡ልብስ፡በብብትኽ፡ከገመዱ፡ በታች፡አድርግ፡አለው፤ኤርምያስም፡እንዲሁ፡አደረገ።
13ኤርምያስንም፡በገመዱ፡ጐተቱት፡ከጕድጓድም፡አወጡት፥ኤርምያስም፡በግዞት፡ቤት፡አደባባይ፡ተቀመጠ።
14ንጉሡም፡ሴዴቅያስ፡ልኮ፡በእግዚአብሔር፡ቤት፡ወደነበረው፡ወደ፡ሦስተኛው፡መግቢያ፡ወደ፡ርሱ፡ ነቢዩን፡ኤርምያስን፡አስመጣው፤ንጉሡም፡ኤርምያስን፦አንዲት፡ነገር፡እጠይቅኻለኹ፤ምንም፡አትሸሽገኝ፡ አለው።
15ኤርምያስም፡ሴዴቅያስን፦ብነግርኽ፡በእውኑ፡አትገድለኝምን፧ብመክርኽም፡አትሰማኝም፡አለው።
16ንጉሡም፡ሴዴቅያስ፦ይህችን፡ነፍስ፡የፈጠረልን፡ሕያው፡እግዚአብሔርን! አልገድልኽም፥ነፍስኽንም፡ ለሚሹ፡ለእነዚህ፡ሰዎች፡እጅ፡አሳልፌ፡አልሰጥኽም፡ብሎ፡በቈይታ፡ለኤርምያስ፡ማለ።
17ኤርምያስም፡ሴዴቅያስን፦የእስራኤል፡አምላክ፡የሰራዊት፡አምላክ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ ይላል፦ወደባቢሎን፡ንጉሥ፡አለቃዎች፡ብትወጣ፥ነፍስኽ፡በሕይወት፡ትኖራለች፡ይህችም፡ከተማ፡በእሳት፡ አትቃጠልም፤አንተም፡ቤትኽም፡በሕይወት፡ትኖራላችኹ።
18ወደባቢሎን፡ንጉሥ፡አለቃዎች፡ባትወጣ፡ግን፥ይህች፡ከተማ፡በከለዳውያን፡እጅ፡ትሰጣለች፥በእሳትም፡ ያቃጥሏታል፡አንተም፡ከእጃቸው፡አታመልጥም፡አለው።
19ንጉሡም፡ሴዴቅያስ፡ኤርምያስን፦ወደ፡ከለዳውያን፡በኰበለሉት፡በአይሁድ፡እጅ፡አሳልፈው፡ይሰጡኛል፡ እነርሱም፡ያፌዙብኛል፡ብዬ፡እፈራለኹ፡አለው።
20ኤርምያስም፡እንዲህ፡አለው፦አሳልፈው፡አይሰጡኽም።እኔ፡የምነግርኽን፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ እባክኽ፥ስማ፤ይቀናኻል፥ነፍስኽም፡በሕይወት፡ትኖራለች።
21ትወጣ፡ዘንድ፡እንቢ፡ብትል፡ግን፥እግዚአብሔር፡ያሳየኝ፡ቃል፡ይህ፡ነው፦
22እንሆ፥በይሁዳ፡ንጉሥ፡ቤት፡የቀሩትን፡ሴቶች፡ዅሉ፡ወደባቢሎን፡ንጉሥ፡አለቃዎች፡ ያወጣሉ፤እነዚያም፡ሴቶች፦ባለሟሎችኽ፡አታ፟ለ፟ውኻል፡አሸንፈውኽማል፤እግሮችኽ፡ግን፡አኹን፡በጭቃ፡ ውስጥ፡ከገቡ፡እነርሱ፡ከአንተ፡ወደ፡ዃላ፡ተመልሰዋል፡ይላሉ።
23ሚስቶችኽንና፡ልጆችኽንም፡ዅሉ፡ወደ፡ከለዳውያን፡ያወጣሉ፤አንተም፡በባቢሎን፡ንጉሥ፡እጅ፡ትያዛለኽ፡ እንጂ፡ከእጃቸው፡አታመልጥም፤ይህችም፡ከተማ፡በእሳት፡ትቃጠላለች።
24ሴዴቅያስም፡ኤርምያስን፡እንዲህ፡አለው፦ይህን፡ቃል፡ማንም፡አይወቅ፥አንተም፡አትሞትም።
25አለቃዎቹ፡ግን፡እኔ፡ከአንተ፡ጋራ፡እንደ፡ተነጋገርኹ፡ቢሰሙ፥ወዳንተም፡መጥተው፦ለንጉሡ፡ ያልኸውን፡ንገረን፡አትሸሽገንም፥እኛም፡አንገድልኽም፤ደግሞ፡ንጉሡ፡ያለኽን፡ንገረን፡ቢሉኽ፥አንተ፦
26በዚያ፡እሞት፡ዘንድ፡ወደዮናታን፡ቤት፡አትመልሰኝ፡ብዬ፡በንጉሡ፡ፊት፡ለመንኹ፡በላቸው።
27አለቃዎቹም፡ዅሉ፡ወደ፡ኤርምያስ፡መጥተው፡ጠየቁ፥ንጉሡም፡እንዳዘዘው፡እንደዚህ፡ቃል፡ዅሉ፡ ነገራቸው።ነገሩም፡አልተሰማምና፡ከርሱ፡ጋራ፡መነጋገርን፡ተው።
28ኢየሩሳሌም፡እስከተያዘችበት፡ቀን፡ድረስ፡በግዞት፡ቤት፡አደባባይ፡ተቀመጠ።