Skip to content
← Jeremiah

Chapter 43 · Amharic

Jeremiah

1የአምላካቸውን፡የእግዚአብሔርን፡ቃል፡ዅሉ፥ለእነርሱ፡አምላካቸው፡እግዚአብሔር፡የላከውን፡ይህን፡ቃል፡ ዅሉ፥ኤርምያስ፡ለሕዝቡ፡ዅሉ፡መናገርን፡በፈጸመ፡ጊዜ፥

2የሆሻያ፡ልጅ፡ዐዛርያስ፡የቃሬያም፡ልጅ፡ዮሐናን፡ትዕቢተኛዎችም፡ሰዎች፡ዅሉ፡ኤርምያስን፦ሐሰት፡ ተናግረኻል፤አምላካችን፡እግዚአብሔር፦በዚያ፡ትቀመጡ፡ዘንድ፡ወደ፡ግብጽ፡አትግቡ፡ብሎ፡አላ፟ከኽም፤

3ነገር፡ግን፥ከለዳውያን፡እንዲገድሉን፡ወደ፡ባቢሎንም፡እንዲማርኩን፡በእጃቸው፡አሳልፈኽ፡ትሰጠን፡ዘንድ፡ የኔርያ፡ልጅ፡ባሮክ፡በላያችን፡ላይ፡አነሣሥቶኻል፡አሉት።

4የቃሬያም፡ልጅ፡ዮሐናን፡የጭፍራ፡አለቃዎችም፡ዅሉ፡ሕዝቡም፡ዅሉ፡በይሁዳ፡ምድር፡ይቀመጡ፡ዘንድ፡ የእግዚአብሔርን፡ቃል፡አልሰሙም።

5የቃሬያም፡ልጅ፡ዮሐናን፡የጭፍራ፡አለቃዎችም፡ዅሉ፡በይሁዳ፡ምድር፡ለመቀመጥ፡ከተሰደዱባቸው፡ ከአሕዛብ፡ዅሉ፡የተመለሱትን፡የይሁዳን፡ቅሬታ፡ዅሉ፥

6ወንዶችንና፡ሴቶችን፡ልጆችንም፡የንጉሡንም፡ሴቶች፡ልጆች፥የዘበኛዎቹም፡አለቃ፡ናቡዘረዳን፡ከሳፋን፡ ልጅ፡ከአኪቃም፡ልጅ፡ከጎዶልያስ፡ጋራ፡የተዋቸውን፡ሰዎች፡ዅሉ፥ነቢዩንም፡ኤርምያስን፡የኔርያንም፡ልጅ፡ ባሮክን፡ወሰዱ፤

7የእግዚአብሔርንም፡ቃል፡አልሰሙምና፡ወደግብጽ፡ምድር፡ገቡ፥እስከ፡ጣፍናስ፡ድረስ፡መጡ።

8በጣፍናስም፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡ወደ፡ኤርምያስ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦

9ታላላቆችን፡ድንጋዮች፡በእጅኽ፡ውሰድ፥የይሁዳም፡ሰዎች፡እያዩ፡በጣፍናስ፡ባለው፡በፈርዖን፡ቤት፡ደጅ፡ መግቢያ፡ሸሽጋቸው፤

10እንዲህም፡በላቸው፦የእስራኤል፡አምላክ፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እንሆ፥ልኬ፡ ባሪያዬን፡የባቢሎንን፡ንጉሥ፡ናቡከደነጾር፡አመጣለኹ፥ዙፋኑንም፡እኔ፡በሸሸግዃቸው፡በእነዚህ፡ድንጋዮች፡ ላይ፡አኖራለኹ፤ርሱም፡ማለፊያውን፡ድንኳኑን፡በላያቸው፡ይዘረጋል።

11መጥቶም፡የግብጽን፡ምድር፡ይመታል፥ለሞትም፡የሚኾነውን፡ለሞት፥ለምርኮም፡የሚኾነውን፡ ለምርኮ፥ለሰይፍም፡የሚኾነውን፡ለሰይፍ፡አሳልፎ፡ይሰጣል።

12በግብጽም፡አማልክት፡ቤቶች፡እሳትን፡ያነዳ፟ል፡ያቃጥላቸውማል፡ይማርካቸውማል፤እረኛም፡ደበሎውን፡ እንደሚደርብ፡እንዲሁ፡የግብጽን፡አገር፡ይደርባል፤ከዚያም፡በሰላም፡ይወጣል።

13በግብጽም፡ምድር፡ያለውን፡የሄልዮቱን፡ከተማ፡ሐውልቶች፡ይሰብራል፥የግብጽንም፡አማልክት፡ቤቶች፡ በእሳት፡ያቃጥላል።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source