Skip to content
← Jeremiah

Chapter 48 · Amharic

Jeremiah

1ስለ፡ሞዐብ፤የእስራኤል፡አምላክ፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ናባው፡ጠፍታለችና፡ ወዮላት! ቂርያታይም፡ዐፍራለች፡ተይዛማለች፤ሚሥጋብ፡ዐፍራለች፡ደንግጣማለች።

2ከእንግዲህ፡ወዲህ፡የሞዐብ፡ትምክሕት፡የለም፤በሐሴቦን፡ላይ፦ኑ፥ሕዝብ፡እንዳትኾን፡እናጥፋት፡ብለው፡ ክፉ፡ነገር፡ዐስበውባታል።መድሜን፡ሆይ፥አንቺ፡ደግሞ፡ትጠፊያለሽ፡ሰይፍም፡ያሳድድሻል።

3መፍረስና፡ታላቅ፡ጥፋት፡የሚል፡የጩኸት፡ቃል፡ከሖሮናይም፡ተሰማ።

4ሞዐብ፡ጠፍታለች፥ልጆቿም፡ጩኸትን፡አሰምተዋል።

5በሉሒት፡ዐቀበት፡ልቅሶ፡እያለቀሱ፡ይወጣሉና፥በሖሮናይምም፡ቍልቍለት፡የጥፋትንና፡የመባባትን፡ጩኸት፡ ሰምተዋል።

6ሸሽታችኹ፡ራሳችኹን፡አድኑ፤በምድረ፡በዳ፡እንዳለ፡ቍጥቋጦ፡ኹኑ።

7በሥራሽና፡በመዝገብሽ፡ታምነሻልና፥አንቺ፡ደግሞ፡ትያዢያለሽ፤ካሞሽም፡ከካህናቱና፡ከአለቃዎቹ፡ጋራ፡ በአንድነት፡ይማረካል።

8እግዚአብሔርም፡እንደ፡ተናገረ፥አጥፊ፡ወደ፡ከተማ፡ዅሉ፡ይመጣል፡አንዲትም፡ከተማ፡ አትድንም፤ሸለቆውም፡ይጠፋል፡ሜዳውም፡ይበላሻል።

9በራ፟፡እንድትወጣ፡ለሞዐብ፡ክንፍ፡ስጧት፤ከተማዎቿም፡ባድማና፡ወና፡ይኾናሉ።

10የእግዚአብሔርን፡ሥራ፡በቸልታ፡የሚያደርግ፡ርጉም፡ይኹን፥ሰይፉንም፡ከደም፡የሚከለክል፡ርጉም፡ ይኹን።

11ሞዐብ፡ከታናሽነቱ፡ዠምሮ፡ቅምጥል፡ነበረ፥በአምቡላውም፡ላይ፡ዐርፏል፥ከዕቃውም፡ወደ፡ዕቃ፡ አልተገላበጠም፥ወደ፡ምርኮም፡አልኼደም፤ስለዚህ፥ቃናው፡በርሱ፡ውስጥ፡ቀርቷል፥መዐዛውም፡ አልተለወጠም።

12ስለዚህ፥እንሆ፥የሚያገላብጡትን፡የምልክበት፡ዘመን፡ይመጣል፥ይላል፡እግዚአብሔር፥እነርሱም፡ ያገላብጡታል፤ጋኖቹንም፡ባዶ፡ያደርጋሉ፥መስቴዎቹንም፡ይሰብራሉ።

13የእስራኤልም፡ቤት፡ይታመንባት፡ከነበረው፡ከቤቴል፡እንዳፈረ፥እንዲሁ፡ሞዐብ፡ከካሞሽ፡ያፍራል።

14እናንተ፦እኛ፡ኀያላን፡በሰልፍም፡ጽኑዓን፡ነን፡እንዴት፡ትላላችኹ፧

15ሞዐብ፡ፈርሷል፥ከተማዎቹም፡ጠፍተዋል፥የተመረጡትም፡ጕልማሳዎች፡ወደ፡መታረድ፡ ወርደዋል፥ይላል፡ስሙ፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡የኾነ፡ንጉሥ።

16የሞዐብ፡ጥፋት፡ሊመጣ፡ቀርቧል፡መከራውም፡እጅግ፡ይፈጥናል።

17በዙሪያው፡ያላችኹ፡ዅሉ፡ስሙንም፡የምታውቁ፡ዅሉ፦ብርቱው፡በትር፥የከበረው፡ሽመል፥እንዴት፡ ተሰበረ! ብላችኹ፡አልቅሱለት።

18በዲቦን፡የምትኖሪ፡ሆይ፥ሞዐብን፡የሚያጠፋ፡ወጥቶብሻልና፥ዐምባሽንም፡ሰብሯልና፥ከክብርሽ፡ ውረጂ፥በጥማትም፡ተቀመጪ።

19በዐሮዔር፡የምትኖሪ፡ሆይ፥በመንገድ፡አጠገብ፡ቆመሽ፡ተመልከቺ፤የሸሸውንና፡ያመለጠችውን፦ምን፡ ኾኗል፧ብለሽ፡ጠይቂ።

20ሞዐብም፡ፈርሷልና፥ዐፈረ፤አልቅሱ፡ጩኹም፤ሞዐብ፡እንደ፡ተዘረፈ፡በአርኖን፡አጠገብ፡አውሩ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

21በሜዳ፡ላይ፥በሖሎን፥በያሳ፥በሜፍዓት፡ላይ፥

22በዲቦን፥በናባው፥በቤት፡ዲብላታይም፡ላይ፥

23በቂርያታይም፥በቤትጋሙል፥

24በቤትምዖን፡ላይ፥በቂርዮት፥በባሶራ፥በሞዐብም፡ምድር፡ከተማዎች፡ዅሉ፡ቅርብና፡ሩቅ፡በኾኑ፡ላይ፡ ፍርድ፡መጥቷል።

25የሞዐብ፡ቀንድ፡ተቈረጠ፡ክንዱም፡ተሰበረ፥ይላል፡እግዚአብሔር።

26በእግዚአብሔር፡ላይ፡ኰርቷልና፥አስክሩት፤ሞዐብም፡በጥፋቱ፡ላይ፡ይንከባለላል፥ደግሞም፡መሳቂያ፡ ይኾናል።

27እስራኤል፡ለአንተ፡መሳቂያ፡አልኾነምን፧ወይስ፡በሌባዎች፡መካከል፡ተገኝቷልን፧ስለ፡ርሱ፡በተናገርኽ፡ ጊዜ፡ራስኽን፡ትነቀንቃለኽ።

28እናንተ፡በሞዐብ፡የምትኖሩ፡ሆይ፥ከተማዎችን፡ትታችኹ፡በአለት፡ውስጥ፡ተቀመጡ፥በገደል፡አፋፍም፡ ቤቷን፡እንደምትሠራ፡እንደ፡ርግብ፡ኹኑ።

29እጅግ፡እንደ፡ታበየ፡ስለሞዐብ፡ትዕቢት፡ስለ፡ትምክሕቱም፡ስለ፡ኵራቱም፡ስለ፡መጓደዱም፡ስለልቡም፡ ትዕቢት፡ሰምተናል።

30ቍጣው፡ምንም፡እንደ፡ኾነ፡ዐውቃለኹ፥ይላል፡እግዚአብሔር፤ፉከራው፡ምንም፡አልሠራም።

31ስለዚህ፥ለሞዐብ፡አለቅሳለኹ፥ለሞዐብም፡ዅሉ፡እጮኻለኹ፤ለቂርሔሬስ፡ሰዎች፡አለቅሳለኹ።

32አንቺ፡የሴባማ፡ወይን፡ሆይ፥ከኢያዜር፡ልቅሶ፡ይልቅ፡ለአንቺ፡አለቅሳለኹ፤ቅርንጫፎችሽ፡ባሕርን፡ ተሻግረዋል፥ወደኢያዜርም፡ባሕር፡ደርሰዋል፤አጥፊው፡በሰብልሽና፡በወይንሽ፡ላይ፡መጥቷል።

33ሐሤትና፡ደስታ፡ከፍሬያማው፡ዕርሻና፡ከሞዐብ፡ምድር፡ጠፍተዋል፤ጠጁን፡ከመጥመቂያው፡ አጥፍቻለኹ፤ጠማቂውም፡በእልልታ፡አይጠምቅም፥እልልታቸውም፡እልልታ፡አይኾንም።

34ከሐሴቦን፡ጩኸት፡እስከ፡ኤልያሊና፡እስከ፡ያሀጽ፡ድረስ፡ድምፃቸውን፡ሰጥተዋል፤ከዞዓር፡እስከ፡ ሖሮናይምና፡እስከ፡ዔግላት፡ሺሊሺያ፡ድረስ፡ይደርሳል፤የኔምሬም፡ውሃ፡ደግሞ፡ይደርቃል።

35በኰረብታው፡መስገጃ፡ላይ፡የሚሠዋውን፡ለአማልክቱም፡የሚያጥነውን፡ከሞዐብ፡አጠፋለኹ፥ይላል፡ እግዚአብሔር።

36ያተረፈው፡ትርፉ፡ጠፍቶበታልና፤ስለዚህ፥ልቤ፡ለሞዐብ፡እንደ፡እንቢልታ፡ይጮኻል፥ልቤም፡ለቂርሔሬስ፡ ሰዎች፡እንደ፡እንቢልታ፡ይጮኻል።

37ራስ፡ዅሉ፡መላጣ፡ጢምም፡ዅሉ፡የተላጨ፡ነውና፤በእጅም፡ዅሉ፡ላይ፡ክትፋት፡በወገብም፡ላይ፡ማቅ፡ አለና።

38ሞዐብን፡እንደማይወደድ፡ዕቃ፡ሰብሬያለኹና፡በሞዐብ፡ሰገነት፡ዅሉ፡ላይ፡በአደባባዩም፡ላይ፡በዅሉም፡ ቦታ፡ልቅሶ፡አለ፥ይላል፡እግዚአብሔር።

39እንዴት፡ተገለበጠ! በዕፍረትም፡የተነሣ፡ሞዐብ፡ዠርባውን፡እንዴት፡መለሰ! ብላችኹ፡አልቅሱ።ሞዐብም፡ በዙሪያው፡ላሉት፡ዅሉ፡መሳቂያና፡ድንጋጤ፡ይኾናል።

40እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላልና፦እንሆ፥እንደ፡ንስር፡ይበራ፟ል፡ክንፉንም፡በሞዐብ፡ላይ፡ይዘረጋል።

41ከተማዎቹ፡ተይዘዋል፥ዐምባዎቹም፡ተወስደዋል፥በዚያም፡ቀን፡የሞዐብ፡ኀያላን፡ልብ፡ምጥ፡እንደ፡ያዛት፡ ሴት፡ልብ፡ይኾናል።

42ሞዐብም፡በእግዚአብሔር፡ላይ፡ኰርቷልና፥ሕዝብ፡ከመኾን፡ይጠፋል።

43በሞዐብ፡የምትኖር፡ሆይ፥ፍርሀትና፡ጕድጓድ፡ወጥመድም፡ባንተ፡ላይ፡አለ፥ይላል፡እግዚአብሔር። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org

44በሞዐብ፡ላይ፡የመጐብኘትን፡ዓመት፡አመጣበታለኹና፥ይላል፡እግዚአብሔር፤በፍርሀት፡የሸሸ፡ በጕድጓድ፡ውስጥ፡ይወድቃል፥ከጕድጓድም፡የወጣ፡በወጥመድ፡ይያዛል።

45የሸሹ፡ደክመው፡ከሐሴቦን፡ጥላ፡በታች፡ቆመዋል፤እሳት፡ከሐሴቦን፡ነበልባልም፡ከሴዎን፡ወጥቷል፡ የሞዐብንም፡ማእዘን፡የሤትንም፡ልጆች፡ዐናት፡በልቷል።

46ሞዐብ፡ሆይ፥ወዮልኽ! የካሞሽ፡ወገን፡ጠፍቷል፤ወንዶች፡ልጆችኽ፡ተማርከዋልና፥ሴቶች፡ልጆችኽም፡ ወደ፡ምርኮ፡ኼደዋልና።

47ነገር፡ግን፥በዃለኛው፡ዘመን፡የሞዐብን፡ምርኮ፡እመልሳለኹ፥ይላል፡እግዚአብሔር።የሞዐብ፡ፍርድ፡ እስከዚህ፡ድረስ፡ነው።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source