1ስለዐሞን፡ልጆች፤እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ለእስራኤል፡ልጆች፡የሉትምን፧ወይስ፡ወራሽ፡ የለውምን፧ስለ፡ምን፡ሚልኮም፡ጋድን፡ወረሰ፧ሕዝቡስ፡በከተማዎቹ፡ላይ፡ስለ፡ምን፡ተቀመጠ፧
2ስለዚህ፥እንሆ፥በዐሞን፡ልጆች፡ከተማ፡በረባት፡ላይ፡የሰልፍ፡ውካታን፡የማሰማበት፡ዘመን፡ ይመጣል፥ይላል፡እግዚአብሔር፤የፍርስራሽ፡ክምርም፡ትኾናለች፥ሴቶች፡ልጆቿም፡በእሳት፡ ይቃጠላሉ፥እስራኤልም፡የወረሱትን፡ይወርሳል፥ይላል፡እግዚአብሔር።
3ሐሴቦን፡ሆይ፥ጋይ፡ፈርሳለችና፡አልቅሺላት፡እናንተም፡የረባት፡ሴቶች፡ልጆች፡ሆይ፥ሚልኮም፡ካህናቱና፡ አለቃዎቹም፡በአንድነት፡ይማረካሉና፡ጩኹ፥ማቅም፡ታጠቁ፥አልቅሱም፥በቅጥሮችም፡መካከል፡ተሯሯጡ።
4ማን፡ይመጣብኛል፡ብለሽ፡በመዝገብሽ፡የታመንሽ፡አንቺ፡ከዳ፟ተኛ፡ልጅ፡ሆይ፥በሸለቆዎችሽ፥ውሃ፡ በሚያረካቸው፡ሸለቆዎችሽ፥ስለ፡ምን፡ትመኪያለሽ፧
5እንሆ፥በዙሪያሽ፡ካሉት፡ዅሉ፡ዘንድ፡ፍርሀትን፡አመጣብሻለኹ፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡ እግዚአብሔር፤እያንዳንዳችኹም፡በፊታችኹ፡ወዳለው፡ስፍራ፡ትሰደዳላችኹ፥የሚሸሹትንም፡የሚሰበስብ፡የለም።
6ነገር፡ግን፥ከዚያ፡በዃላ፡የዐሞንን፡ልጆች፡ምርኮ፡እመልሳለኹ፥ይላል፡እግዚአብሔር።
7ስለ፡ኤዶምያስ፤የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በእውኑ፡በቴማን፡ጥበብ፡ የለምን፧ከብልኀተኛዎችስ፡ምክር፡ጠፍቷልን፧
8ጥበባቸውስ፡አልቋልን፧እናንተ፡በድዳን፡የምትኖሩ፡ሆይ፥የዔሳውን፡ጥፋት፥የምጐበኝበትን፡ ጊዜ፥አመጣበታለኹና፡ሽሹ፥ወደ፡ዃላ፡ተመለሱ፥በጥልቅም፡ውስጥ፡ተቀመጡ።
9ወይን፡ለቃሚዎች፡ቢመጡብኽ፥ቃርሚያውን፡አይተውልኽምን፧ሌባዎችስ፡በሌሊት፡ቢመጡ፥የሚያጠፉት፡ እስኪበቃቸው፡ድረስ፡አይደለምን፧
10እኔ፡ግን፡ዔሳውን፡ዐራቈትኹት፥የተሸሸጉትንም፡ስፍራዎች፡ገለጥኹ፥ይሸሸግም፡ዘንድ፡ አይችልም፤ዘሩም፡ወንድሞቹም፡ጎረቤቶቹም፡ጠፍተዋል፡ርሱም፡የለም።
11ድኻ፡አደጎችኽን፡ተው፥እኔም፡በሕይወት፡አኖራቸዋለኹ፤መበለቶችኽም፡በእኔ፡ይታመኑ።
12እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላልና፦እንሆ፥ጽዋውን፡ያልተገባቸው፡ሰዎች፡ጠጥተውታል፤አንተም፡ሳትቀጣ፡ ትቀራለኽን፧በርግጥ፡ትጠጣለኽ፡እንጂ፡ያለቅጣት፡አትቀርም።
13ባሶራ፡መደነቂያና፡መሰደቢያ፡መረገሚያም፡እንድትኾን፡በራሴ፡ምያለኹ፥ይላል፡ እግዚአብሔር፤ከተማዎቿም፡ዅሉ፡ለዘለዓለም፡ባድማ፡ይኾናሉ።
14ከእግዚአብሔር፡ዘንድ፡ወሬ፡ሰምቻለኹ፡በአሕዛብም፡መካከል።ተሰብሰቡ፥በርሷም፡ላይ፡ኑ፡ለሰልፍም፡ ተነሡ፡የሚል፡መልእክተኛ፡ተልኳል።
15እንሆ፥በአሕዛብ፡ዘንድ፡የተጠቃኽ፥በሰዎችም፡ዘንድ፡የተናቅኽ፡አድርጌኻለኹ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
16በአለት፡ንቃቃት፡ውስጥ፡የምትቀመጥ፥የተራራውን፡ከፍታ፡የምትይዝ፡ሆይ፥ድፍረትኽና፡የልብኽ፡ ኵራት፡አታለ፟ውኻል።ቤትኽን፡ምንም፡እንደ፡ንስር፡ከፍ፡ብታደርግ፥ከዚያ፡አወርድኻለኹ፥ይላል፡ እግዚአብሔር።
17ኤዶምያስም፡መደነቂያ፡ትኾናለች፥የሚያልፍባትም፡ዅሉ፡ይደነቃል፥ስለመጣባትም፡መቅሠፍት፡ዅሉ፡ ያፏጭባታል።
18ሰዶምና፡ገሞራ፡በእነርሱም፡አጠገብ፡የነበሩት፡ከተማዎች፡እንደ፡ተገለበጡ፥ይላል፡ እግዚአብሔር፥እንዲሁ፡በዚያ፡ሰው፡አይቀመጥም፡የሰው፡ልጅም፡አይኖርባትም።
19እንሆ፥ከርሷ፡ዘንድ፡በቶሎ፡አባርራቸዋለኹና፡በጠነከረው፡ዐምባ፡ላይ፡ከዮርዳኖስ፡ትዕቢት፡ውስጥ፡ እንደ፡አንበሳ፡ይወጣል፤የተመረጠውንም፡በርሷ፡ላይ፡እሾመዋለኹ፤እንደ፡እኔ፡ያለ፡ማን፡ነው፧ወይስ፡ ለእኔ፡ጊዜ፡የሚወስን፡ማን፡ነው፧ወይስ፡ፊቴን፡የሚቃወም፡እረኛ፡ማን፡ነው፧
20ስለዚህ፥እግዚአብሔር፡በኤዶምያስ፡ላይ፡የመከረባትን፡ምክር፥በቴማንም፡በሚኖሩ፡ሰዎች፡ላይ፡ያሰባትን፡ ዐሳብ፡ስሙ፤በእውነት፡የመንጋ፡ትንንሾች፡ይጐተታሉ፤በእውነት፡ማደሪያቸውን፡ባድማ፡ያደርግባቸዋል።
21ከመውደቃቸው፡ድምፅ፡የተነሣ፡ምድር፡ተናወጠች፥የጩኸታቸውም፡ድምፅ፡በቀይ፡ባሕር፡ተሰማ።
22እንሆ፥እንደ፡ንስር፡ወጥቶ፡ይበራል፡ክንፉንም፡በባሶራ፡ላይ፡ይዘረጋል፥በዚያም፡ቀን፡የኤዶምያስ፡ ኀያላን፡ልብ፡ምጥ፡እንደ፡ያዛት፡ሴት፡ልብ፡ይኾናል።
23ስለ፡ደማስቆ፤ክፉ፡ወሬ፡ሰምተዋልና፥ሐማትና፡አርፋድ፡ዐፈሩ፥ቀለጡም፤በባሕርም፡ላይ፡ሐዘን፡ አለ፥ታርፍም፡ዘንድ፡አትችልም።
24ደማስቆ፡ደከመች፡ትሸሽም፡ዘንድ፡ዘወር፡አለች፡እንቅጥቅጥም፡ያዛት፥እንደ፡ወላድም፡ሴት፡ጣርና፡ ምጥ፡ያዛት።
25የተመሰገነችው፡ከተማ፥የደስታዬ፡ከተማ፥ሳትለቀቅ፡እንዴት፡ቀረች፧
26ስለዚህ፥ጐበዛዝቷ፡በአደባባይዋ፡ላይ፡ይወድቃሉ፥በዚያም፡ቀን፡ሰልፈኛዎች፡ዅሉ፡ይጠፋሉ፥ይላል፡ የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር።
27በደማስቆም፡ቅጥር፡ላይ፡እሳት፡አነዳ፟ለኹ፡የወልደ፡አዴርንም፡አዳራሾች፡ትበላለች።
28የባቢሎን፡ንጉሥ፡ናቡከደነጾር፡ስለ፡መታ፡ስለቄዳርና፡ስለአሶር፡መንግሥታት፤እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ ይላል፦ተነሡ፡ወደ፡ቄዳርም፡ውጡ፥የምሥራቅንም፡ልጆች፡አጥፉ።
29ድንኳናቸውንና፡መንጋቸውን፡ይወስዳሉ፤መጋረጃዎቻቸውንና፡ዕቃቸውን፡ዅሉ፡ግመሎቻቸውንም፡ ለራሳቸው፡ይወስዳሉ፥በዙሪያቸውም፡ዅሉ፡ጥፋትን፡ጥሩባቸው።
30እናንተ፡በአሶር፡የምትኖሩ፡ሆይ፥የባቢሎን፡ንጉሥ፡ናቡከደነጾር፡ተማክሮባችዃልና፥ዐሳብም፡ ዐስቦባችዃልና፥ሽሹ፥ወደ፡ሩቅም፡ኺዱ፥በጥልቅም፡ውስጥ፡ተቀመጡ፥ይላል፡እግዚአብሔር።
31ተነሡ፥ዕርፊት፡ወዳለበት፡ተዘልሎም፡ወደተቀመጠው፥ደጅና፡መወርወሪያ፡ወደሌለው፡ብቻውንም፡ ወደተቀመጠው፡ሕዝብ፡ውጡ።
32ግመሎቻቸው፡ይበዘበዛሉ፡የእንስሳዎቻቸውም፡ብዛት፡ይማረካል፤ጠጕራቸውንም፡በዙሪያ፡የሚላጩትን፡ ሰዎች፡ወደ፡ነፋሳት፡ዅሉ፡እበትናቸዋለኹ፤ከዳርቻቸውም፡ዅሉ፡ጥፋት፡አመጣባቸዋለኹ፥ይላል፡ እግዚአብሔር።
33አሶርም፡የቀበሮ፡መኖሪያና፡የዘለዓለም፡ባድማ፡ትኾናለች፤በዚያም፡ሰው፡አይኖርም፥የሰው፡ልጅም፡ አይቀመጥባትም።
34በይሁዳ፡ንጉሥ፡በሴዴቅያስ፡መንግሥት፡መዠመሪያ፡ስለ፡ዔላም፡ወደ፡ነቢዩ፡ወደ፡ኤርምያስ፡ የመጣው፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡ይህ፡ነው፦ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
35የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እንሆ፥ዋና፡የኀይላቸው፡መሣሪያ፡የኾነውን፡የዔላምን፡ ቀስት፡እሰብራለኹ።
36ከአራቱም፡ከሰማይ፡ማእዘናት፡አራቱን፡ነፋሳት፡በዔላም፡ላይ፡አመጣለኹ፥ወደ፡እነዚያም፡ነፋሳት፡ዅሉ፡ እበትናቸዋለኹ፤ከዔላም፡የተሰደዱ፡ሰዎች፡የማይደርሱበት፡ሕዝብ፡አይገኝም።
37በጠላቶቻቸውና፡ነፍሳቸውን፡በሚሿት፡ፊት፡ዔላምን፡አስደነግጣለኹ፤ክፉ፡ነገርን፡ርሱም፡ጽኑ፡ቍጣዬን፡ አመጣባቸዋለኹ፥ይላል፡እግዚአብሔር፤እስካጠፋቸውም፡ድረስ፡በዃላቸው፡ሰይፍ፡እሰድ፟ባቸዋለኹ፤
38ዙፋኔንም፡በዔላም፡አኖራለኹ፥ከዚያም፡ንጉሡንና፡አለቃዎቹን፡አጠፋለኹ፥ይላል፡እግዚአብሔር።
39ነገር፡ግን፥በዃለኛው፡ዘመን፡የዔላምን፡ምርኮ፡እመልሳለኹ፥ይላል፡እግዚአብሔር።