1ከሴት፡የተወለደ፡ሰው፡ የሕይወቱ፡ዘመን፡ጥቂት፡ቀን፡ነው፥መከራም፡ይሞላዋል።
2እንደ፡አበባ፡ይወጣል፥ይረግፋልም፤ እንደ፡ጥላም፡ይሸሻል፥ርሱም፡አይጸናም።
3እንደዚህስ፡ባለ፡ሰው፡ላይ፡ዐይኖችኽን፡ትከፍታለኽን፧ ከአንተስ፡ጋራ፡እኔን፡ወደ፡ፍርድ፡ታገባለኽን፧
4ከርኩስ፡ነገር፡ንጹሕን፡ሊያወጣ፡ማን፡ይችላል፧ አንድ፡እንኳ፡የሚችል፡የለም።
5የሰው፡ዕድሜ፡የተወሰነ፡ነው፥ የወሩም፡ቍጥር፡ባንተ፡ዘንድ፡ነው፥ ርሱም፡ሊተላለፈው፡የማይችለውን፡ዳርቻ፡አደረግኽለት።
6እንደ፡ምንደኛ፡ዕድሜው፡እስኪፈጸም፡ድረስ፡ ያርፍ፡ዘንድ፡ከርሱ፡ጥቂት፡ዘወር፡በል።
7ዛፍ፡ቢቈረጥ፡ደግሞ፡ያቈጠቍጥ፡ዘንድ፥ ቅርንጫፉም፡እንዳያልቅ፡ተስፋ፡አለው።
8ሥሩም፡በምድር፡ውስጥ፡ቢያረጅ፥ ግንዱም፡በመሬት፡ውስጥ፡ቢሞት፥
9ከውሃ፡ሽታ፡የተነሣ፡ያቈጠቍጣል፤ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org እንደ፡አትክልት፡ቅርንጫፍ፡ያወጣል።
10ሰው፡ግን፡ይሞትና፡ይጋደማል፤ ሰውም፡ነፍሱን፡ይሰጣል፥ርሱስ፡ወዴት፡አለ፧
11ውሃ፡ከባሕር፡ውስጥ፡ያልቃል፤ ወንዙም፡ያንሳል፡ይደርቅማል።
12ሰውም፡ተኝቶ፡አይነሣም፤ ሰማይ፡እስኪያልፍ፡ድረስ፡አይነቃም፥ ከእንቅልፉም፡አይነሣም።
13በሲኦል፡ውስጥ፡ምነው፡በሰወርኸኝ፡ኖሮ! ቍጣኽ፡እስኪያልፍ፡ድረስ፡በሸሸግኸኝ፡ኖሮ! ቀጠሮም፡አድርገኽ፡ምነው፡ባሰብኸኝ፡ኖሮ!
14በእውኑ፡ሰው፡ከሞተ፡ተመልሶ፡ሕያው፡ይኾናልን፧ መለወጤ፡እስኪመጣ፡ድረስ፥ የሰልፌን፡ዘመን፡ዅሉ፡በትዕግሥት፡በተጠባበቅኹ፡ነበር።
15በጠራኸኝና፡በመለስኹልኽ፡ነበር፤ የእጅኽንም፡ሥራ፡በተመኘኸው፡ነበር።
16አኹን፡ግን፡ርምጃዬን፡ቈጥረኸዋል፤ ኀጢአቴንም፡ትጠባበቃለኽ።
17መተላልፌ፡በከረጢት፡ውስጥ፡ታትሟል፥ ኀጢአቴንም፡ለብጠኽበታል።
18ተራራ፡ሲወድቅ፡ይጠፋል፥ አለቱም፡ከስፍራው፡ይፈልሳል፤
19ውሃዎች፡ድንጋዮቹን፡ይፍቃሉ፤ ፈሳሾቹም፡የምድሩን፡ዐፈር፡ይወስዳሉ፤ እንዲሁ፡የሰውን፡ተስፋ፡ታጠፋዋለኽ።
20ለዘለዓለም፡ታሸንፈዋለኽ፥ርሱም፡ያልፋል፤ ፊቱን፡ትለውጣለኽ፥ርሱንም፡ትሰደ፟ዋለኽ።
21ልጆቹ፡ቢከብሩ፡አያውቅም፤ ቢዋረዱም፡አያይም።
22ነገር፡ግን፥የገዛ፡ሥጋው፡ሕመም፡ብቻ፡ይሰማዋል፥ ለራሱም፡ብቻ፡ያለቅሳል።