1ዅሉን፡ከሚችል፡አምላክ፡ዘንድ፡ዘመናት፡አልተሰወረምና፡ ርሱን፡የሚያውቁ፡ለምን፡ወራቱን፡አያዩም፧
2የድንበሩን፡ምልክት፡የሚያፈርሱ፡አሉ፤ መንጋዎቹን፡በዝብዘው፡ያሰማራሉ።
3የድኻ፡አደጎቹን፡አህያ፡ይነዳሉ፤ የመበለቲቱን፡በሬ፡ስለ፡መያዣ፡ይወስዳሉ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
4ድኻዎቹን፡ከመንገዱ፡ያወጣሉ፤ የምድርም፡ችግረኛዎች፡ዅሉ፡ይሸሸጋሉ።
5እንሆ፥በምድረ፡በዳ፡እንዳሉ፡እንደ፡ሜዳ፡አህያዎች፥ መብልን፡ፈልገው፡ወደ፡ሥራቸው፡ይወጣሉ፤ ምድረ፡በዳውም፡ለልጆቻቸው፡መብልን፡ይሰጣቸዋል።
6እነዚያ፡በዕርሻ፡ውስጥ፡እኽላቸውን፡ያጭዳሉ፤ የበደለኛውንም፡ወይን፡ይቃርማሉ።
7ዕራቍታቸውን፡ያለልብስ፡ያድራሉ፥ በብርድ፡ጊዜ፡መጐናጸፊያ፡የላቸውም።
8ከተራራዎች፡በሚወርድ፡ዝናብ፡ይረጥባሉ፤ መጠጊያም፡ዐጥተው፡ቋጥኙን፡ያቅፋሉ።
9ድኻ፡አደጉን፡ልጅ፡ከጡቱ፡የሚነጥሉ፡አሉ፡ ከችግረኛውም፡መያዣ፡ይወስዳሉ።
10ያለ፡ልብስ፡ዕራቍታቸውን፡ይኼዳሉ፤ ተርበውም፡ነዶዎችን፡ይሸከማሉ፤
11በእነዚህ፡ሰዎች፡ዐጥር፡ውስጥ፡ዘይት፡ያደርጋሉ፤ ወይንም፡ይጠምቃሉ፥ነገር፡ግን፥ይጠማሉ።
12ከከተማውና፡ከገዛ፡ቤቶቻቸው፡ይባረራሉ፤ የልጆችም፡ነፍስ፡ለርዳታ፡ትጮኻለች፤ እግዚአብሔር፡ግን፡ስንፍናቸውን፡አይመለከትም።
13እነዚህ፡በብርሃን፡ላይ፡የሚያምፁ፡ናቸው፤ መንገዱን፡አያውቁም፥በጐዳናውም፡አይጸኑም።
14ነፍሰ፡ገዳዩም፡ሳይነጋ፡ማልዶ፡ይነሣል፤ ችግረኛዎችንና፡ድኻዎችን፡ይገድላል፤ በሌሊትም፡እንደ፡ሌባ፡ነው።
15የአመንዝራም፡ዐይን፡ድግዝግዝታን፡ይጠብቃል። የማንም፡ዐይን፡አያየኝም፡ይላል፥ ፊቱንም፡ይሸፍናል።
16ቤቶቹን፡በጨለማ፡ይነድላሉ፤ በቀን፡ይሸሸጋሉ፤ ብርሃንም፡አያውቁም።
17የጧት፡ብርሃን፡ለእነርሱ፡ዅሉ፡እንደ፡ሞት፡ጥላ፡ነው፤ የሞትን፡ጥላ፡ድንጋጤ፡ያውቃሉና። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
18እነርሱ፡በውሃ፡ፊት፡ላይ፡በረ፟ው፡ያልፋሉ፤ ዕድል፡ፈንታቸውም፡በምድር፡ላይ፡የተረገመች፡ናት፤ ወደ፡ወይኑ፡ቦታ፡መንገድ፡አይዞሩም።
19ድርቅና፡ሙቀት፡የዐመዳዩን፡ውሃ፡ያጠፋሉ፤ እንዲሁ፡ሲኦል፡በደለኛዎችን፡ታጠፋለች።
20ማሕፀን፡ትረሳዋለች፤ ትልም፡በደስታ፡ይጠባዋል፤ ዳግመኛም፡አይታሰብም፤ ክፋትም፡እንደ፡ዛፍ፡ይሰበራል።
21የማትወልደውን፡መካኒቱን፡ይበድላታል፤ ለመበለቲቱም፡በጎነት፡አያደርግም።
22ነገር፡ግን፥በኀይሉ፡ኀያላንን፡ይስባል፤ ርሱም፡በተነሣ፡ጊዜ፡ሰው፡በሕይወቱ፡አይታመንም።
23እግዚአብሔር፡በደኅና፡አኑሯቸዋል፥ በዚያም፡ይታመናሉ፤ ዐይኖቹ፡ግን፡በመንገዳቸው፡ላይ፡ናቸው።
24ጥቂት፡ጊዜ፡ከፍ፡ከፍ፡ይላሉ፤ ይኼዳሉ፥ይጠወልጋሉም፤ እንደ፡ሌላዎች፡ዅሉ፡ይከማቻሉ፤ እንደ፡እሸትም፡ራስ፡ይቈረጣሉ።
25እንዲህስ፡ባይኾን፡ሐሰተኛ፡የሚያደርገኝ፥ ነገሬንስ፡እንደ፡ምናምን፡የሚያደርገው፡ማን፡ነው፧