Skip to content
← Job

Chapter 4 · Amharic

Job

1ቴማናዊውም፡ኤልፋዝ፡መለሰ፡እንዲህም፡አለ፦

2አንድ፡ሰው፡ከአንተ፡ጋራ፡ይናገር፡ዘንድ፡ቢሞክር፡ትቀየማለኽን፧ ቃልንስ፡ከመናገር፡ሊቀር፡የሚችል፡ማን፡ነው፧

3እንሆ፥አንተ፡ብዙዎችን፡ታስተምር፡ነበር፥ የደከሙትንም፡እጆች፡ታበረታ፡ነበር፥

4ቃልኽ፡የሚሰናከለውን፡ያስነሣ፡ነበር፥ አንተም፡የሚብረከረከውን፡ጕልበት፡ታጸና፡ነበር።

5አኹን፡ግን፡ባንተ፡ላይ፡መጥቷል፥አንተም፡ደከምኽ፤ ደርሶብኻል፥አንተም፡ተቸገርኽ።

6አምላክኽን፡መፍራትኽ፡መጽናናትኽ፥ የቅንነትኽም፡መንገድ፡ተስፋኽ፡አይደለምን፧

7እባክኽ፡ዐስብ፥ንጹሕ፡ኾኖ፡የጠፋ፡ማን፡ነው፧ ከልበ፡ቅንስ፡የተደመሰሰ፡ማን፡ነው፧

8እኔ፡እንዳየኹ፥ኀጢአትን፡የሚያርሱ፥ መከራንም፡የሚዘሩ፡ይህንኑ፡ያጭዳሉ።

9በእግዚአብሔር፡እስትንፋስ፡ይጠፋሉ፥ በቍጣውም፡መንፈስ፡ያልቃሉ።

10የአንበሳ፡ጩኸት፥የጯኺ፡አንበሳ፡ድምፅ፥ የአንበሳ፡ደቦል፡ጥርስ፡ተሰባበረ።

11አሮጌ፡አንበሳ፡አደን፡በማጣት፡ይሞታል፥ የአንበሳዪቱም፡ግልገሎች፡ይበተናሉ።

12ለኔም፡በምስጢር፡ቃል፡መጣልኝ፥ ዦሮዬም፡ሹክሹክታውን፡ሰማች።

13በሌሊት፡ሕልም፡ዐሳብ፡ሲነሣ፥ የከበደም፡እንቅልፍ፡በሰው፡ላይ፡ሲወድቅ፥

14ዐጥንቴን፡ዅሉ፡ያናወጡ፡ ድንጋጤና፡መንቀጥቀጥ፡ወደቁብኝ።

15መንፈስም፡በፊቴ፡ዐለፈ፤ የሥጋዬ፡ጠጕር፡ቆመ።

16ርሱም፡ቆመ፥መልኩን፡ግን፡ለመለየት፡አልቻልኹም፥ ምሳሌም፡በዐይኔ፡ፊት፡ነበረ፤ የዝምታ፡ድምፅ፡ሰማኹ።

17በእውኑ፡ሰው፡በእግዚአብሔር፡ፊት፡ጻድቅ፡ሊኾን፥ http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org ወይስ፡ሰው፡በፈጣሪው፡ፊት፡ሊነጻ፡ይችላልን፧

18እንሆ፥በባሪያዎቹ፡አይታመንም፤ መላእክቱንም፡ስንፍና፡ይከሳ፟ቸዋል፤

19ይልቁንስ፡በጭቃ፡ቤት፡የሚኖሩ፥ መሠረታቸው፡በትቢያ፡ውስጥ፡የኾነ፥ ከብል፡በፊት፡የሚጨፈለቁ፡እንዴት፡ይኾኑ፧

20በጧትና፡በማታ፡መካከል፡ይሰባበራሉ፤ ማንም፡ሳያስብ፡ለዘለዓለም፡ይጠፋሉ።

21ገመዳቸው፡የተነቀለ፡አይደለምን፧ አለጥበብም፡ይሞታሉ።

Amharic — extracted from the Ethiopian Orthodox typeset edition (Desta Unicode), lossless; verify symbols against the source