1እንሆ፥መልእክተኛዬን፡እልካለኹ፥መንገድንም፡በፊቴ፡ያስተካክላል፤እናንተም፡የምትፈልጉት፡ጌታ፡ በድንገት፡ወደ፡መቅደሱ፡ይመጣል፤የምትወዱትም፡የቃል፡ኪዳን፡መልእክተኛ፥እንሆ፥ይመጣል፥ይላል፡ የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር።
2ነገር፡ግን፥ርሱ፡እንደ፡አንጥረኛ፡እሳትና፡እንደ፡ዐጣቢ፡ሳሙና፡ነውና፥የሚመጣበትን፡ቀን፡መታገሥ፡ የሚችል፡ማን፡ነው፧ርሱስ፡በተገለጠ፡ጊዜ፡የሚቆም፡ማን፡ነው፧
3ርሱም፡ብርን፡እንደሚያነጥርና፡እንደሚያጠራ፡ሰው፡ይቀመጣል፥የሌዊንም፡ልጆች፡ያጠራል፥እንደ፡ ወርቅና፡እንደ፡ብርም፡ያነጥራቸዋል፤እነርሱም፡ለእግዚአብሔር፡በጽድቅ፡ቍርባንን፡የሚያቀርቡ፡ይኾናሉ።
4እግዚአብሔርም፡እንደ፡ዱሮው፡ዘመንና፡እንደ፡ቀደሙት፡ዓመታት፡በይሁዳና፡በኢየሩሳሌም፡ቍርባን፡ ደስ፡ይለዋል።
5ለፍርድ፡ወደ፡እናንተ፡እቀርባለኹ፤በመተተኛዎችና፡በአመንዝራዎች፥በሐሰትም፡በሚምሉ፥የምንደኛውን፡ ደመ፡ወዝ፡በሚከለክሉ፥መበለቲቱንና፡ድኻ፡አደጉን፡በሚያስጨንቁ፥የመጻተኛውንም፡ፍርድ፡ በሚያጣምሙ፥እኔንም፡በማይፈሩ፡ላይ፡ፈጣን፡ምስክር፡እኾንባቸዋለኹ፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር።
6እኔ፡እግዚአብሔር፡አልለወጥም፤እናንተ፡የያዕቆብ፡ልጆች፡ሆይ፥ስለዚህ፡የጠፋችኹ፡አይደላችኹም።
7ከአባቶቻችኹ፡ዘመን፡ዠምር፡ከሥርዐቴ፡ፈቀቅ፡ብላችዃል፥ርሷንም፡አልጠበቃችኹም፦ወደ፡እኔ፡ ተመለሱ፥እኔም፡ወደ፡እናንተ፡እመለሳለኹ፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር።እናንተ፡ ግን፦የምንመለሰው፡በምንድር፡ነው፧ብላችዃል።
8ሰው፡እግዚአብሔርን፡ይሰርቃልን፧እናንተ፡ግን፡እኔን፡ሰርቃችዃል።እናንተም፦የሰረቅንኽ፡በምንድር፡ ነው፧ብላችዃል።በዓሥራትና፡በበኵራት፡ነው።
9እናንተ፥ይህ፡ሕዝብ፡ዅሉ፥እኔን፡ሰርቃችዃልና፥በርግማን፡ርጉሞች፡ናችኹ።
10በቤቴ፡ውስጥ፡መብል፡እንዲኾን፡ዓሥራቱን፡ዅሉ፡ወደ፡ጐተራ፡አግቡ፤የሰማይንም፡መስኮት፡ ባልከፍትላችኹ፥በረከትንም፡አትረፍርፌ፡ባላፈስ፟ላችኹ፡በዚህ፡ፈትኑኝ፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር።
11ስለ፡እናንተ፡ነቀዙን፡እገሥጻለኹ፥የምድራችኹንም፡ፍሬ፡አያጠፋም፤በዕርሻችኹም፡ያለው፡ወይን፡ ፍሬውን፡አያረግፍም፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር።
12የተድላ፡ምድር፡ትኾናላችኹና፡አሕዛብ፡ዅሉ፡ብፁዓን፡ብለው፡ይጠሯችዃል፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡ እግዚአብሔር።
13ቃላችኹ፡በእኔ፡ላይ፡ድፍረት፡ኾኗል፥ይላል፡እግዚአብሔር።እናንተ፡ግን፦ባንተ፡ላይ፡ደፍረን፡ የተናገርነው፡በምንድር፡ነው፧ብላችዃል።
14እናንተም፦እግዚአብሔርን፡ማገልገል፡ከንቱ፡ነው፤ትእዛዙንስ፡በመጠበቅ፥በሰራዊት፡ጌታ፡ በእግዚአብሔር፡ፊት፡ሐዘንተኛዎች፡ኾነን፡በመኼድ፡ምን፡ይረባናል፧
15አኹንም፡የሚታበዩትን፡ሰዎች፡ብፁዓን፡ብለን፡እንጠራቸዋለን፤ክፉንም፡የሚሠሩ፡ጸንተዋል፡ እግዚአብሔርንም፡ይፈታተናሉ፥ያመልጣሉም፡ብላችዃል።
16የዚያን፡ጊዜ፡እግዚአብሔርን፡የሚፈሩ፡ርስ፡በርሳቸው፡ተነጋገሩ፤እግዚአብሔርም፡ አደመጠ፥ሰማም፥እግዚአብሔርንም፡ለሚፈሩ፡ስሙንም፡ለሚያስቡ፡የመታሰቢያ፡መጽሐፍ፡በፊቱ፡ተጻፈ።
17እኔ፡በምሠራበት፡ቀን፡እነርሱ፡የእኔ፡ገንዘብ፡ይኾናሉ፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፤ሰውም፡ የሚያገለግለውን፡ልጁን፡እንደሚምር፥እንዲሁ፡እምራቸዋለኹ።
18ተመልሳችኹም፡በጻድቁና፡በኀጢአተኛው፡መካከል፥ለእግዚአብሔር፡በሚገዛውና፡በማይገዛው፡መካከል፡ ትለያላችኹ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org