1በንጉሡ፡በአርጤክስስ፡በኻያኛው፡ዓመት፡በኒሳን፡ወር፡የወይን፡ጠጅ፡በፊቱ፡በነበረ፡ጊዜ፡ጠጁን፡ አንሥቼ፡ለንጉሡ፡ሰጠኹት።ቀድሞ፡ግን፡በፊቱ፡ያለሐዘን፡እኖር፡ነበር።
2ንጉሡም፦ሳትታመም፡ፊትኽ፡ለምን፡ዐዘነ፧ይህ፡የልብ፡ሐዘን፡ነው፡እንጂ፡ሌላ፡ነገር፡አይደለም፡ አለኝ።እጅግም፡ብዙ፡አድርጌ፡ፈራኹ።
3ንጉሡንም፦ንጉሡ፡ሺሕ፡ዓመት፡ይንገሥ፤የአባቶቼ፡መቃብር፡ያለባት፡ከተማ፡ተፈታ፟ለችና፥በሮቿም፡ በእሳት፡ተቃጥለዋልና፥ፊቴ፡ስለ፡ምን፡አይዘን፧አልኹት።
4ንጉሡም፦ምን፡ትለምነኛለኽ፧አለኝ።እኔም፡ወደሰማይ፡አምላክ፡ጸለይኹ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
5ንጉሡንም፦ንጉሡን፡ደስ፡ቢያሠኝኽ፥ባሪያኽም፡በፊትኽ፡ሞገስ፡ቢያገኝ፥እሠራው፡ዘንድ፡ወደ፡ይሁዳ፡ ወዳባቶቼ፡መቃብር፡ከተማ፡ስደደኝ፡አልኹት።
6ንግሥቲቱም፡በአጠገቡ፡ተቀምጣ፡ሳለች፡ንጉሡ፦መንገድኽ፡እስከ፡መቼ፡ድረስ፡ይኾናል፧መቼስ፡ ትመለሳለኽ፧አለኝ።ንጉሡም፡ይሰደ፟ኝ፡ዘንድ፡ደስ፡አለው፤እኔም፡ዘመኑን፡ቀጠርኹለት።
7ንጉሡንም፦ንጉሡ፡ደስ፡ቢለው፥እስከይሁዳ፡አገር፡እንዲያደርሱኝ፡በወንዝ፡ማዶ፡ላሉት፡ገዢዎች፡ ደብዳቤ፡ይሰጠኝ፤
8በቤቱም፡አጠገብ፡ላለው፡ለግንብ፡በሮች፥ለከተማውም፡ቅጥር፥ለምገባበትም፡ቤት፡ዕንጨት፡እንዲሰጠኝ፡ ለንጉሡ፡ዱር፡ጠባቂ፡ለአሣፍ፡ደብዳቤ፡ይሰጠኝ፡አልኹት።ንጉሡም፡በእኔ፡ላይ፡መልካም፡እንደ፡ኾነችው፡ እንደ፡አምላኬ፡እጅ፡ሰጠኝ።
9በወንዙም፡ማዶ፡ወዳሉት፡አለቃዎች፡መጥቼ፡የንጉሡን፡ደብዳቤ፡ሰጠዃቸው፡ንጉሡም፡ከእኔ፡ጋራ፡ የሰራዊቱን፡አለቃዎችና፡ፈረሰኛዎች፡ሰደደ።
10ሖሮናዊውም፡ሰንባላጥና፡ባሪያው፡አሞናዊ፡ጦብያ፡ለእስራኤል፡ልጆች፡መልካምን፡ነገር፡የሚሻ፡ሰው፡ እንደ፡መጣ፡በሰሙ፡ጊዜ፡እጅግ፡ተበሳጩ።
11ወደ፡ኢየሩሳሌምም፡ደረስኹ፥በዚያም፡ሦስት፡ቀን፡ያኽል፡ተቀመጥኹ።
12በሌሊትም፡ተነሣኹ፥ከእኔም፡ጋራ፡ዐያሌ፡ሰዎች፡ነበሩ፤እግዚአብሔርም፡ለኢየሩሳሌም፡ኣደርገው፡ዘንድ፡ በልቤ፡ያኖረውን፡ለማንም፡አላስታወቅኹም፤ተቀምጬበት፡ከነበረው፡እንስሳ፡በቀር፡ከእኔ፡ጋራ፡ምንም፡እንስሳ፡ አልነበረም።
13በሸለቆውም፡በር፡ወጣኹ፥ወደዘንዶውም፡ምንጭና፡ወደጕድፍ፡መጣያው፡በር፡ኼድኹ፤የፈረሰውንም፡ የኢየሩሳሌምን፡ቅጥር፥በእሳትም፡የተቃጠሉትን፡በሮቿን፡ተመለከትኹ።
14ወደምንጩም፡በርና፡ወደንጉሡ፡መዋኛ፡ዐለፍኹ፤ተቀምጬበትም፡የነበረው፡እንስሳ፡የሚያልፍበት፡ ስፍራ፡አልነበረም።
15በሌሊትም፡በፈፋው፡በኩል፡ወጥቼ፡ቅጥሩን፡ተመለከትኹ፤ዘወርም፡ብዬ፡በሸለቆው፡በር፡ ገባኹ፥እንዲሁም፡ተመለስኹ።
16ሹማምቱ፡ግን፡ወዴት፡እንደ፡ኼድኹ፥ምን፡እንዳደረግኹም፡አላወቁም፡ነበር፤ለአይሁድና፡ ለካህናቱ፥ለታላላቆችና፡ለሹማምቱም፥ሥራም፡ይሠሩ፡ለነበሩት፡ለሌላዎች፡ገና፡አልተናገርኹም፡ነበር።
17እኔም፦እኛ፡ያለንበትን፡ጕስቍልና፡ኢየሩሳሌም፡እንደ፡ፈረሰች፥በሮቿም፡በእሳት፡እንደ፡ተቃጠሉ፡ ታያላችኹ፤አኹንም፡ከእንግዲህ፡ወዲህ፡መሳለቂያ፡እንዳንኾን፡ኑና፡የኢየሩሳሌምን፡ቅጥር፡እንሥራ፡ አልዃቸው።
18የአምላኬም፡እጅ፡በእኔ፡ላይ፡መልካም፡እንደ፡ኾነች፥ንጉሡም፡የነገረኝን፡ቃል፡ ነገርዃቸው።እነርሱም፦እንነሣና፡እንሥራ፡አሉ።እጃቸውንም፡ለበጎ፡ሥራ፡አበረቱ።
19ሖሮናዊውም፡ሰንባላጥ፥ባሪያውም፡አሞናዊው፡ጦብያ፥ዐረባዊውም፡ጌሳም፡በሰሙ፡ጊዜ፥በንቀት፡ ሣቁብን፤ቀላል፡አድርገውንም፦ይህ፡የምታደርጉት፡ነገር፡ምንድር፡ነው፧በእውኑ፡በንጉሡ፡ላይ፡ትሸፍቱ፡ ዘንድ፡ትወዳ፟ላችኹን፧አሉ።
20እኔም፡መልሼ፦የሰማይ፡አምላክ፡ያከናውንልናል፥እኛም፡ባሪያዎቹ፡ተነሥተን፡እንሠራለን፤እናንተ፡ግን፡ በኢየሩሳሌም፡ዕድል፡ፈንታና፡መብት፡መታሰቢያም፡የላችኹም፡አልዃቸው።