1ተመልሼም፡ዐይኖቼን፡አነሣኹ፥እንሆም፥አንድ፡በራሪ፡የመጽሐፍ፡ጥቅል፟፡አየኹ።
2ርሱም፦የምታየው፡ምንድር፡ነው፧አለኝ።እኔም፦በራሪ፡የመጽሐፍ፡ጥቅል፟፡አያለኹ፤ርዝመቱ፡ኻያ፡ ክንድ፡ወርዱም፡ዐሥር፡ክንድ፡ነው፡አልኹ።
3እንዲህም፡አለኝ፦ይህ፡በምድር፡ፊት፡ዅሉ፡ላይ፡የሚወጣው፡ርግማን፡ነው፤የሚሰርቅ፡ዅሉ፡በርሱ፡ ላይ፡በዚህ፡በኩል፡እንደተጻፈው፡ዅሉ፡ይጠፋል፥በሐሰት፡የሚምልም፡ዅሉ፡በርሱ፡ላይ፡በዚያ፡በኩል፡ እንደተጻፈው፡ዅሉ፡ይጠፋል።
4እኔ፡አስወጣዋለኹ፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፥ወደሚሰርቀውም፡ቤት፥በሐሰትም፡በስሜ፡ ወደሚምለው፡ቤት፡ይገባል፤በቤቱም፡ውስጥ፡ይኖራል፥ርሱንም፥ዕንጨቱንና፡ድንጋዩን፥ይበላል።
5ከእኔም፡ጋራ፡ይነጋገር፡የነበረው፡መልአክ፡ወጥቶ፦ዐይኖችኽን፡አንሣ፥ይህችም፡የምትወጣው፡ምን፡ እንደ፡ኾነች፡እይ፡አለኝ።
6እኔም፦ምንድር፡ናት፧አልኹ።ርሱም፦ይህች፡የምትወጣው፡የኢፍ፡መስፈሪያ፡ናት፡ አለኝ።ደግሞም፦በምድር፡ዅሉ፡ላይ፡ያለ፡በደላቸው፡ይህ፡ነው፡አለ።
7እንሆም፥የርሳሱን፡መክሊት፡አነሡት፤እንሆም፥በኢፍ፡መስፈሪያው፡ውስጥ፡አንዲት፡ሴት፡ተቀምጣ፡ ነበር።
8ርሱም፦ይህች፡ክፋት፡ናት፡አለኝ፤በኢፍ፡መስፈሪያው፡ውስጥ፡ጣላት፥የርሳሱንም፡ጠገራ፡በመስፈሪያ፡ አፍ፡ላይ፡ጣለ።
9ዐይኖቼንም፡አንሥቼ፡አየኹ፥እንሆም፥ኹለት፡ሴቶች፡ወጡ፥ነፋስም፡በክንፎቻቸው፡ነበረ፤ክንፎቻቸውም፡ እንደ፡ሽመላ፡ክንፎች፡ነበሩ፤የኢፍ፡መስፈሪያውንም፡በምድርና፡በሰማይ፡መካከል፡አነሡት።
10ከእኔም፡ጋራ፡ይነጋገር፡የነበረውን፡መልአክ፦እነዚህ፡የኢፍ፡መስፈሪያውን፡ወዴት፡ ይወስዱታል፧አልኹት።
11ርሱም፦በሰናዖር፡ምድር፡ቤት፡ይሠሩለት፡ዘንድ፡ይወስዱታል፤በተዘጋጀም፡ጊዜ፡በዚያ፡በስፍራው፡ ይኖራል፡አለኝ።