1የሰራዊትም፡ጌታ፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡ወደ፡እኔ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
2የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ስለ፡ጽዮን፡ታላቅ፡ቅንአት፡ቀንቻለኹ፥በታላቅም፡ቍጣ፡ ስለ፡ርሷ፡ቀንቻለኹ።
3እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ወደ፡ጽዮን፡ተመልሻለኹ፥በኢየሩሳሌምም፡መካከል፡ እኖራለኹ፤ኢየሩሳሌምም፡የእውነት፡ከተማ፡ትባላለች፤የሰራዊትም፡ጌታ፡የእግዚአብሔር፡ተራራ፡የተቀደሰ፡ ተራራ፡ይባላል።
4የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦ዳግመኛ፡ሽማግሌዎችና፡ባልቴቶች፡በኢየሩሳሌም፡ አደባባይ፡ይቀመጣሉ፤ሰውም፡ዅሉ፡ከዕድሜው፡ብዛት፡የተነሣ፡ምርኵዝ፡በእጁ፡ይይዛል።
5የከተማዪቱም፡አደባባዮች፡በእነዚያ፡በሚጫወቱ፡ወንዶችና፡ሴቶች፡ልጆች፡ይሞላሉ።
6የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በዚህ፡ወራት፡በዚህ፡ሕዝብ፡ቅሬታ፡ዐይን፡ዘንድ፡ድንቅ፡ ቢኾን፥በእውኑ፡በእኔ፡ዐይን፡ዘንድ፡ደግሞ፡ድንቅ፡ይኾናልን፧ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር።
7የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦እንሆ፥ሕዝቤን፡ከምሥራቅ፡ምድርና፡ከምዕራብ፡ምድር፡ አድነዋለኹ፤
8አመጣቸዋለኹም፥በኢየሩሳሌምም፡ውስጥ፡ይኖራሉ፤እነርሱም፡ሕዝብ፡ይኾኑኛል፥እኔም፡በእውነትና፡ በጽድቅ፡አምላክ፡እኾናቸዋለኹ።
9የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦መቅደሱ፡ይሠራ፡ዘንድ፡የሰራዊት፡ጌታ፡የእግዚአብሔር፡ ቤት፡ከተመሠረተበት፡ቀን፡ዠምሮ፡ከነቢያት፡አፍ፡ይህን፡ቃል፡በዚህ፡ዘመን፡የሰማችኹ፡እናንተ፡ ሆይ፥እጃችኹን፡አበርቱ።
10ከዚያ፡ወራት፡አስቀድሞ፡ለሰውና፡ለእንስሳ፡ዋጋ፡አልነበረምና፤እኔም፡ሰውን፡ዅሉ፡በወንድሙ፡ላይ፡ አስነሥቼ፡ነበርና፥ካስጨናቂው፡የተነሣ፡ለሚገባውና፡ለሚወጣው፡ሰላም፡አልነበረም።
11አኹን፡ግን፡እንደ፡ቀደመው፡ዘመን፡በዚህ፡ሕዝብ፡ቅሬታ፡ላይ፡አልኾንም፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡ እግዚአብሔር።
12ነገር፡ግን፥ሰላምን፡እዘራለኹ፤ወይኑ፡ፍሬውን፡ይሰጣል፥ምድርም፡አዝመራዋን፡ታወጣለች፥ሰማያትም፡ ጠላቸውን፡ይሰጣሉ፤ለዚህም፡ሕዝብ፡ቅሬታ፡ይህን፡ነገር፡ዅሉ፡አወርሳለኹ። http://www.gzamargna.net www.ethiopianorthodox.org
13የይሁዳ፡ቤትና፡የእስራኤል፡ቤት፡ሆይ፥በአሕዛብ፡ዘንድ፡ርግማን፡እንደ፡ነበራችኹ፥እንዲሁ፡ አድናችዃለኹ፥በረከትም፡ትኾናላችኹ፤አትፍሩ፥እጃችኹንም፡አበርቱ።
14የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላልና፦አባቶቻችኹ፡እጅግ፡ባስቈጡኝ፡ጊዜ፡ክፉ፡ለማድረግ፡ እንዳሰብኹ፥እንዳልተጸጸትኹም፥ይላል፡የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፥
15እንዲሁ፡ዳግመኛ፡ለኢየሩሳሌምና፡ለይሁዳ፡ቤት፡በዚህ፡ወራት፡በጎነትን፡ኣደርግ፡ዘንድ፡ ዐስቤያለኹ፤አትፍሩ።
16የምትሠሩት፡ነገር፡ይህ፡ነው፤እያንዳንዳችኹ፡ከባልንጀራችኹ፡ጋራ፡እውነትን፡ተነጋገሩ፤በበር፡ አደባባያችኹም፡የእውነትንና፡የሰላምን፡ፍርድ፡ፍረዱ፤
17ዅላችኹም፡በባልንጀራችኹ፡ላይ፡ክፉን፡ነገር፡በልባችኹ፡አታስቡ፤የሐሰትንም፡መሐላ፡ አትውደዱ፤ይህን፡ነገር፡ዅሉ፡እጠላለኹና፥ይላል፡እግዚአብሔር።
18የሰራዊት፡ጌታ፡የእግዚአብሔር፡ቃል፡ወደ፡እኔ፡እንዲህ፡ሲል፡መጣ፦
19የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦የአራተኛው፡ወር፡ጾም፡የዐምስተኛውም፡የሰባተኛውም፡ የዐሥረኛውም፡ወር፡ጾም፡ለይሁዳ፡ቤት፡ደስታና፡ተድላ፡የሐሤትም፡በዓላት፡ይኾናል፤ስለዚህም፡እውነትንና፡ ሰላምን፡ውደዱ።
20የሰራዊት፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በብዙ፡ከተማዎች፡የሚቀመጡ፡አሕዛብ፡ገና፡ይመጣሉ፤
21በአንዲትም፡ከተማ፡የሚኖሩ፡ሰዎች፦እግዚአብሔርን፡እንለምን፡ዘንድ፥የሰራዊትንም፡ጌታ፡ እግዚአብሔርን፡እንፈልግ፡ዘንድ፡ኑ፡እንኺድ፤እኔም፡እኼዳለኹ፡እያሉ፡ወደ፡ሌላ፡ከተማ፡ይኼዳሉ።
22ብዙ፡ወገኖችና፡ኀይለኛዎች፡አሕዛብ፡በኢየሩሳሌም፡የሰራዊትን፡ጌታ፡እግዚአብሔርን፡ይፈልጉ፡ ዘንድ፥እግዚአብሔርንም፡ይለምኑ፡ዘንድ፡ይመጣሉ።
23የሰራዊትም፡ጌታ፡እግዚአብሔር፡እንዲህ፡ይላል፦በዚያ፡ዘመን፡ከአሕዛብ፡ቋንቋ፡ዅሉ፡ዐሥር፡ሰዎች፡ የአንዱን፡አይሁዳዊ፡ሰው፡ልብስ፡ዘርፍ፡ይዘው፦እግዚአብሔር፡ከእናንተ፡ጋራ፡እንዳለ፡ሰምተናልና፥ከእናንተ፡ ጋራ፡እንኺድ፡ይላሉ።